የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በምክር ቤቱ ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጡ።
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ 6ኛ መደበኛ ስብሰባውን እያካሄደ ይገኛል። በዚሁ ስብሰባ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን የሥራ አፈጻጸም በሚመለከት ከምክር ቤት አባላት በርካታ ጥያቄዎች ቀርበዋል።
ከምክር ቤት አባላቱ ከተነሱት ዋና ዋና ጥያቄዎች መካከል ከጎረቤት ሀገራት ጀምሮ እስከ ዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከናወኑ ያሉ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራዎች፣ የቆንስላ ጽሕፈት ቤት አገልግሎቶችን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተደራሽ የማድረግ አስፈላጊነት እንዲሁም በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተከብሮ እንዲሠሩ እየተደረገ ያለው ክትትል የሚሉት ይገኙበታል።
በተጨማሪም በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች የሀገሪቱን የባሕር በር ፍላጎት ለማሳካት እያከናወኑት ያለው ተግባር ተጠይቋል።
በተለይም ከቀጣናዊ ትስስር ጋር በተያያዘ የሀገሪቱን የባሕር በር ባለቤትነት ለማረጋገጥ ተቋሙ ምን ያህል ርቀት እንደሄደ የሚጠይቁና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በምክር ቤት አባላቱ ተነስተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ የፐብሊክ ዲፕሎማሲን በሚመለከት ከሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በመቀናጀት ውጤታማ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም፣ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበርና የዜጎችን መብት ለማስጠበቅ የሚደረገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መናገራቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።