ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት በከተሞች ብቻ ሳይሆን በገጠር አካባቢዎችም ፕላንን መሠረት ያደረገ ዕድገት ማስመዝገብ እንደሚገባ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።
ሚኒስትሯ "በፕላን የተሠሩ የገጠር ማዕከላት፤ በአንድ ወረዳ አንድ የገጠር ማዕከል" በሚል መሪ ሃሳብ በሆሳዕና ከተማ በተካሄደ ሀገር አቀፍ መድረክ ላይ፤ የገጠር ማዕከላት ነገ ከተማ እንደሚሆኑ አውቆ በመንቀሳቀስ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ቤቶችና በፕላን የሚመሩ ግንባታዎችን ማከናወን እንደሚገባ አሳስበዋል።
አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል በገጠር የሚኖር በመሆኑ፣ ደረጃውን የጠበቀ የመኖሪያ ቤትና መሠረተ ልማት የተሟላለት አካባቢ በመፍጠር ብልፅግናን ማረጋገጥ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የመደመር መንግሥት ለከተሞች ትኩረት በመስጠት የቤቶችን ፖሊሲና ስትራቴጂ በመቅረጽ ውጤታማ ሥራዎች እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማትና ኢንዱስትሪ አስተባባሪና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤል በበኩላቸው፤ የመድረኩ ዓላማ የከተማና ገጠር ትስስርን በመሠረተ ልማት ማጠናከር መሆኑን ገልጸዋል።
በንቅናቄ መድረኩ የፌዴራል፣ የክልልና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንቶች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በስንታየሁ ወልደሚካኤል