Search

ከኢኮኖሚው ባለፈ የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ ምቹ የሆነው የኢትዮጵያ ቡና

ማክሰኞ ታኅሣሥ 21, 2018 164

የቱሪዝም ሚኒስቴር ያዘጋጀው የቡና ቱሪዝም የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የትውውቅ ጉዞ መርሐ ግብር እየተከናወነ ይገኛል።
መርሐ ግብሩ ኢትዮጵያውያን ከቡና ጋር ያላቸውን ጥልቅ የባህል ቁርኝት በማሳየት፣ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ግንባር ቀደም ተመራጭነት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማስተዋወቅ ያለመ መሆኑ ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ ቡና በሁሉም የዓለም ክፍሎች ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለው በመሆኑ፣ ከምርት እስከ ግብይት ያለውን ሂደት ለዓለም ማስተዋወቅ አስፈላጊ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ወይኒቱ መልኩ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የቡና መገኛ በመሆኗ በዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም ለዓለም ለማስተዋወቅ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ቡናን መሰረት ያደረገው የትውውቅ ጉዞ እንደ ጅማ፣ ከፋ፣ ሲዳማ እና ይርጋጨፌ ያሉ ዋና ዋና የቡና አምራች አካባቢዎችን ያካተተ ሲሆን፤ በጉዞው ላይ የሚሳተፉ ጋዜጠኞችም ከቡና ለቀማ እና ዝግጅት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን በመመልከት ስለ ቡና ቱሪዝም ግንዛቤ እንዲኖራቸው የሚያስችል መሆኑ ተጠቁሟል።
መርሐ ግብሩ እስከ ታኅሣሥ 25 ቀን 2018 ዓ.ም የሚቀጥል ሲሆን፤ ዛሬ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዴኦ ዞን ገደብ ወረዳ የቡና ማሳ የመስክ ጉብኝት ተካሂዷል።
ቡና የኢትዮጵያውያን መገለጫ ከመሆኑ ባለፈ፣ ማኅበራዊ ትስስርን በማጠናከር ረገድ ዘመናትን የተሻገረ እሴት በመሆኑ፤ ይህን ትልቅ የሀገር ሀብት ለዓለም ገልጦ ማሳየትና ማስተዋወቅ እንደሚገባም ተገልጿል።
በአሚር ጌቱ