Search

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ለሲንቄ ኢንቨስትመንት ባንክ የሥራ ፈቃድ ሰጠ

ረቡዕ ታኅሣሥ 22, 2018 193

ሲንቄ ኢንቨስትመንት ባንክ በኢትዮጵያ አምስተኛው የኢንቨስትመንት ባንክ ሆኖ የሥራ ፈቃድ ማግኘቱን የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን አስታወቀ።
የኢንቨስትመንት ባንኩ ከ480 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ይዞ መቋቋሙን የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተኸልቁ ገልጸዋል።
በመድረኩ የተገኙት የሲንቄ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ ነዋይ መገርሳ ለኢንዱስትሪው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ ደንበኞች በአማራጭ የሚጠቀሙባቸውን መድረኮች ለመፍጠር በጋራ እንደሚሠሩ አስታውቀዋል።
የሲንቄ ኢንቨስትመንት ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ግርማ ሙለታ በበኩላቸው፤ ተቋሙ የካፒታል ገበያ ሥራን እውን በማድረግ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ብሎም ተወዳዳሪነትን ለመጨመር እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
ሲንቄ ኢንቨስትመንት ባንክ የኢትዮጵያን የሰነደ መዋዕለ ንዋይ ግብይት እንቅስቃሴ በማጎልበት እና የማማከር አገልግሎት ከመስጠት አንጻር የራሱ የሆነ አይነተኛ ሚና እንደሚኖረው ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ሲንቄ ኢንቨስትመንት ባንክን ጨምሮ እስካሁን ለ15 ተቋማት የሥራ ፈቃድ ሰጥቷል።
 
በብሩክታዊት አስራት