የባንኩ የማኔጅመንት አባላት በተሰበሰቡበት ዛሬ ይፋ በተደረገው መረጃ መሠረት፥ ባንኩ በ2025/26 በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ ብቻ ከ325 ቢሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ተቀማጭ በመሰብሰብ አጠቃላይ ተቀማጩን 2 ትሪሊዮን ብር አድርሷል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት ተወካይ እና የኮርፖሬት አገልግሎቶች ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ፥ ባንኩ 3 ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አጠቃላይ ተቀማጩን በእጥፍ በማሳደግ 2 ትሪሊዮን ብር ማድረሱን ተናግረዋል።
አቶ ኤፍሬም፥ አፈፃፀሙ የ2030 የባንኩ ስትራቴጂ ውጤት መሆኑን እና ይህም ለባንኩ ትልቅ ስኬት መሆኑን በመግለፅ፤ ለስኬቱ መገኘት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የነበራቸውን ሪጅኖች፣ ዲቪዥኖች፣ ዲስትሪክቶች እንዲሁም መላውን ሠራተኛ እና ደንበኞችን ጭምር አመስግነዋል።
ስኬቱ በቀጣዮቹ 6 ወራትም የተሻለ ለመሥራት እንደሚያነሳሳ እና በበጀት ዓመቱ መጨረሻ 750 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ተቀማጭ ለማሰባሰብ ታልሞ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም ሁሉም የባንኩ ማኔጅመንትና ሠራተኞች፣ የነበሩ ድክመቶችን በማረምና ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል እንዲሠሩ አቶ ኤፍሬም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቢዝነስ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ደረጀ ፉፋ በበኩላቸው፥ ባንኩ በ34 ወራት ውስጥ የትሪሊዮን ብስራትን መድገሙን አስታውሰው፤ ከባንኩ ሪጅኖች እስከ ቅርንጫፎች ለዚህ ስኬት ለመብቃት በርካታ ውጣ ውረዶች መታለፋቸውን ጠቁመዋል።
አቶ ደረጀ አክለውም፥ በበጀት ዓመቱ 6 ወራት ብቻ የተገኘው ተቀማጭ ገንዘብ፣ በየወቅቱ አቅማችንን በእጥፍ እያሳደግን ለመምጣታችን ማሳያ ነው ብለዋል።
ከዚህ የላቀ ስኬት ለማምጣት ሁሉም በጋራ እንዲሠራም የሥራ ሃላፊዎቹ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
#EBC #ebcdotstream #CBE