Search

ኢትዮጵያ በሴራ የተነፈገችው የባሕር በር

ዓርብ ጥር 01, 2018 60

የታሪክ ምሁራን የኤርትራን መገንጠል እና የኢትዮጵያ የባሕር በር ማጣትን ሲያነሡ በወቅቱ ራስ ገዝ አስተዳደር ስለነበረችው የአሰብ ወደብ እና ስለመከነው ዕድል አብረው ያነሣሉ።
የደርግ መንግሥት የአስተዳደር ዘመኑ ሊያበቃ ሦስት ዓመታት ሲቀሩት የአስተዳደር ንድፉን አስተካክሎት እንደነበር አይዘነጋም።
ይህ ማስተካከያ የአሰብ ወደብን ራስ ገዝ በማድረግ ኢትዮጵያ የባሕር መዳረሻዋ እንዲረጋገጥ የሚያደርግ ነበር።
ሆኖም የኢትዮጵያ ንግድ እና ዋና የሎጂስቲክስ ማዕከል በመሆን ራስ ገዝ የነበረችው አሰብ ተላልፋ እንድትሰጥ መደረጉ የመከነ ዕድል ስለመሆኑ በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአውሮፓ እና አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል ዳርእስከዳር ታዬ (ዶ/ር) ያስረዳሉ።
በተለይም ኤርትራ የሀገርነት እውቅናን ስታገኝ ኢትዮጵያን ሲያስተዳድር የነበረው የሽግግር መንግሥት የባሕር በር አማራጭ እንዲመቻች አለራሰመጠየቁ ቀዳሚው ስህተት ስለመሆኑ አስታውሰው ከዚያም በኋላ የባሕር በር አማራጭ የሚገኝበት አስቻይ ሁኔታ እንደነበር ለኢቲቪ ተናግረዋል።
በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት የነበረውን የአሸናፊነት ብልጫ በመጠቀም የባሕር በር አማራጭ ይስተካከልን የሚለውን አጀንዳ በማንሣት፣ የትውልዱን ጥያቄ ማስመለስ የሚቻል ቢሆንም የብሔራዊ ጥቅምን ያልተገነዘቡ አካላት ያን ማድረግ ስላለመቻላቸው ገልጸው ዕድሉ ስለመባከኑ አክለዋል።
እነዚህ የባከኑ ዕድሎች ኢትዮጵያን ከተፈጥሯዊ ስጦታዋ ነጥለው መልከ ብዙ የሆኑ ችግሮችን እንድትጋፈጥ አድርገዋታል ይላሉ።
ኢ-ፍትሐዊነት፣ የሉዓላዊ ግዛት ማጣት፣ የባሕር በር አማራጭ ያለመኖር እና ተገማች ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ያስተናገደችው ኢትዮጵያ ይህ እንዲያበቃ የሚያስችለውን የመደመር ትውልድ ጥያቄዋን ማንሳቷንም አመላክተዋል።
ይህም በተጠና እና ኃላፊነት በተላበሰ መልኩ የሚቀጥል ነው። የመደመር ትውልድ ያነሣውን የባሕር በር የይገባኛል ጥያቄን ማሳካቱ አይቀሬ ነው።
 
በአፎሚያ ክበበው