የፌዴራል መስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር እና የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አብርሃም በላይ (ዶ/ር)፣ ከሶማሊ ክልል የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ ሹክሪና ከሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን የተጠናቀቁ የፕሮጀክት ሥራዎች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
ኃላፊዎቹ በጉብኝታቸው ወቅት የሸበሌ ሪዞርት ፕሮጀክት የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ መጠናቀቁን ያረጋገጡ ሲሆን፣ ለምረቃ ሥነ ሥርዓት እየተደረገ ያለውን ዝግጅትም ተመልክተዋል።
በተጨማሪም፣ በፕሮጀክቱ ግንባታ ምክንያት ከሥፍራው ለተነሱ አነስተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተጎብኝተዋል።
ይህም የመደመር መንግሥት ለተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎችና በልማት ፕሮጀክቶች ምክንያት ተጽዕኖ ለሚያርፍባቸው ወገኖች ቅድሚያ የመስጠት ፖሊሲ አካል መሆኑ ተገልጿል።
ከባለሙያዎችና ፕሮጀክቱን ከሚያከናውኑ ድርጅቶች ጋር በመሆን የተለያዩ የፕሮጀክቱን ክፍሎች ተዘዋውረው የተመለከቱት ኃላፊዎቹ፣ የኮንስትራክሽን ድርጅቶቹ ባለፉት ወራት ላከናወኑት መልካም የሥራ አፈጻጸም ምስጋና ማቅረባቸውን የሶማሊ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመለክታል።