Search

በቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት የሚሳተፉ የዓለማችን ታዋቂ ኩባንያዎች

ሰኞ ጥር 04, 2018 760

ከትናንት በስቲያ ግንባታው በይፋ የተጀመረው የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ከሕንጻ ዲዛይን ጀምሮ የፕሮጀክቱ አማካሪና ተቆጣጣሪ በመሆን የሚሠሩት በሥነ-ሕንጻ ስመ-ጥር የሆኑ ግዙፍ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ናቸው።

ከዓለማችን ትላልቅ የአውሮፕላን ማረፊያዎች አንዱ በሆነው እና በአፍሪካ ተወዳዳሪ በሌለው የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ግንባታ ከሚሳተፉ ኩባንያዎች መካከል ዛሃ ሃዲድ እና ፓስካል ዋትሰን በዲዛይን እና መሰል ሥራዎች የተሳተፉ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱን የማማከር እና የመቆጣጠር ሥራው ደግሞ ዳር አል-ሃንዳሳ በተባለ የሥነ-ሕንጻና የኢንጂነሪንግ ኩባንያ የሚመራ ይሆናል።

ከተመሠረተ 70 ዓመታትን ያስቆጠረው ዳር አል-ሃንዳሳ ኩባንያ 60 ሀገራት ውስጥ 9 ሺህ 250 በላይ ሠራተኞች ያሉት ግዙፍ ድርጅት ሲሆን፤ 70 ዓመታት ታሪኩ 540 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው 4 ሺህ 500 በላይ ፕሮጀክቶችን ማከናወን የቻለ ኩባንያ ነው።

በኢትዮጵያም ከወራት በፊት ግንባታው የተጀመረውና በርዝመቱ በአፍሪካ ተወዳዳሪ የሌለውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሕንጻ ግንባታን የማማከርና የመቆጣጠር ሥራ የያዘው ይህ ግዙፍ ድርጅት ነው።

በቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ዲዛይንና መሰል ሥራዎች ላይ የተሳተፈው ሌላው ታዋቂ ኩባንያ ዛሃ ሃዲድ አርክቴክትስ ነው። ድርጅቱ .. 1980 የተመሠረተ ሲሆን፤ 44 ሀገራት በመቶዎች የሚቆጠሩ ልዩ እና ዘመናዊ ዲዛይን ያላቸው ፕሮጀክቶችን በማከናወን የተሳካለት ኩባንያ መሆኑን አስመስክሯል።

በሥነ-ሕንጻ ጥበባቸው የረቀቀ ውበትን የተላበሱ ዘመናዊ ሕንጻዎችን በመገንባት የታወቀው ይህ ኩባንያ፣ ከዓለማችን ትላልቅ የአውሮፕላን ማረፊያዎች መካከል የሚመደበውን የቻይና ቤይጂንግ ዳክሲንግ አውሮፕላን ማረፊያን፣ የአዘርባጃኑን ሄይዳር አሊዬቭ ሴንተር፣ በቻይና ጓንግዙ የሚገኘውን የኦፔራ ማዕከል እና በጣሊያን ሮም የሚገኘውን የማክሲ ሙዚየምን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ያስረከበ ስኬታማ ድርጅት ነው።

ሌላኛው ከዛሃ ሃዲድ ጋር በመሆን የአዲሱን አውሮፕላን ማረፊያ የግንባታ ንድፍ የሠራው ኩባንያ ዋና መሥሪያ ቤቱን በእንግሊዝ ያደረገው ፓስካል ዋትሰን ነው።

70 ዓመታት የካበተ ልምድ ያለው ይህ ኩባንያ በአየርላንድ የሚገኘውን የደብሊን አውሮፕላን ማረፊያ፣ በሳውዲ ሪያድ የሚገኘውን የንጉሥ አብዱልአዚዝ አውሮፕላን ማረፊያ እና የሪያድ የሜትሮ ባቡር መስመር ግንባታን ጨምሮ በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ያከናወነ ነው።

 

በዋሲሁን ተስፋዬ

 

#EBCDotstream #Ethiopia #BishoftuInternationalAirport #ZahaHadid #PascallWatson #daralhandasah