Search

የውኃ ደኅንነት እና ኢትዮጵያ

ሰኞ ጥር 04, 2018 473

ዓለማችን ችግሯም ሆነ ስኬቷ የሚቀዳው ከጠብታ ውኃ እስከ ባሕር ውኃ ባለው ፖለቲካ ነው ቢባል ልክ ለመሆኑ ብዙ ምክንያቶችን ማቅረብ ይቻላል።

በእርግጥ ውኃ ምንድን ነው ቢባል ይህ ነው ብሎ ለመመለስም አዳጋች ያደረገው እና ዛሬም ድረስ ሀገራት የአቅማቸውም የፍላጎታቸውም መዳረሻ ያደረጉት ውኃን ነው። ዋናው ነገር የውኃ መያዣው ነው። ጠብታም ይሁን የባሕር ውኃ የዓለም ጉዳይ መሆኑ አይቀርም ደግሞም አልቀረም።

ዓለም 2026 ‘ውኃን ከማቅረብ’ ‘የውኃ ደኅንነትን ማረጋገጥወደሚል መርህ ትኩረቷን ቀይራለች፡፡ የውኃን ደኅንነት ከማኅበራዊ ፍትህ እና ከውኃ ደኅንነት አስፈላጊነት ጋር የሚገናኝ ነው።

በቅርቡ በዱባይ የተካሄደው 2026 የተባበሩት መንግሥታት የውኃ ኮንፈረንስ ላይ እንደተነሳው የውኃ አቅርቦት እና ደኅንነት የማይነጣጠሉ ጽንሰ ሀሳቦች ናቸው።

ውኃ በዓለም ላይ እየተስፋፋ ለመጣው የአየር ንብረት ለውጥ ፈተና ተጋላጭ ከሆነ ደኅንነቱን የተጠበቀ ውኃ ማግኘት አዳጋች እንደሚሆን ነው በኮንፈረንሱ ላይ የተጠቀሰው፡፡

የውኃ ደኅንነት አደጋ ላይ የሚወድቅ ከሆነ ደግሞ ፍትሃዊ የውኃ ተደራሽነት ሊኖር አይችልም፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ዓለም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የውኃ ደኅንነት ላይ ዋና ትኩረቱን አድርጎ እየሠራ ያለው፡፡

በዓለም ጤና ድርጅት መስፈርት መሰረት የውኃ ደኅንነት መረጋገጥ ያለበት በውኃ ደኅንነት ዕቅዶች (WSPs) አማካኝነት እንደሆነ ይጠቀሳል። የውኃ ደኅንነት ዕቅድ ዋና መርህም "ከተፋሰስ እስከ ተጠቃሚ" የሚል ሲሆን፣ ውኃ ከምንጬ ጀምሮ እስከ ተጠቃሚው ድረስ ደኅንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን የሚሠራበት ነው፡፡

የደኅንነት እርምጃዎቹ በትክክል እየሠሩ መሆናቸውን እና ውኃው ለሰዎች ጤና ተስማሚ መሆኑን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተከታታይ የክትትል ሥራዎችም አስፈላጊዎች ናቸው።

የውኃን ደኅንነት ቧንቧው ላይ ከመሞከር ይልቅ ገና በተፋሰስ ላይ እያለ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እና ጥበቃ ማድረግ ዋና ሥራ መሆን አለበት፡፡ ውኃው በሚያልፍባቸው መስመሮች ላይ ክትትል እና አስፈላጊውን የደኅንነት መጠበቂያ ሥራዎች መሥራት ያስፈልጋል፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ሀገራት ውኃ ላይ የሚከሰቱ ኬሚካላዊ እና ባዮሎጂያዊ ለውጦችን ለመመርመር እንደ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ያሉ የዘመኑ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ጀምረዋል።

የውኃ ፍትሃዊነት ሰዎች በማንኛውም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግባቸው ለመኖር መሰረታዊ የሆነውን ውኃ በትክክል ማግኘታቸውን ማረጋገጥ ነው። ፍትሃዊነት ማለት የውኃ ዋጋ የአንድን ሰው ውኃ የማግኘት መብት ሳይከለክል ውኃን ለመሰረታዊ ፍላጎቱ ማግኘት ነው።

እያንዳንዱ ሰው በቂ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ የጤናማነት ደረጃውን ያረጋገጠ ውኃ በቅርብ እና ተመጣጣኝ በሆነ የአገልግሎት ክፍያ ብቻ የማግኘት መብት እንዳለው ዓለም አቀፍ እና የሀገራት ሕጎች ደንግገዋል።

ተደራሽነቱ ሴቶች እና ህጻናትን እንዲሁም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎችንም ታሳቢ ያደረገ መሆን እንዳለበት በውኃ ኮንፈረንሶች ላይ በተደጋጋሚ ተነስቷል፡፡

በተያዘው የፈረንጆች ዓመት የውኃ ፕሮጀክቶች 90 በመቶ ለሚሆኑት የከተማ ነዋሪዎች ንጹህ ውኃን ቢያቀርቡ እንኳን ቀሪው 10 በመቶ ተጋላጭ ከሆነ እንደ ውጤታማነት እንደማይቆጠር የዓለም ጤና ድርጅት ያስቀመጠው መስፈርት ያመላክታል። በዚህም መሰረት ፍትሃዊነት ደኅንነት ሲጣመሩ የውኃ አቅርቦት ስኬት መለኪያ ይሆናሉ።

ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ምን እየሠራች ነው?

ኢትዮጵያ በአፍሪካ የተጠና የውኃ ስትራቴጂ አውጥተው ተግባራዊ እያደረጉ ካሉ ሀገራት አንዷ ነች። የውኃ መሰረተ ልማቶች የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችሉ እና ደኅንነቱን የጠበቀ ውኃ የሚያቀርቡ እንዲሆኑ ታሳቢ ተደርገው እየተሠሩ ናቸው።

ኢትዮጵያ ይህን ደኅንነቱን የጠበቀ ውኃ የማዳረስ ስትራቴጂዋን ተግባራዊ ለማድረግ በዘርፉ ከተሰማሩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየሠራች ትገኛለች፡፡

በአፍሪካ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል የውኃ ደኅንነት እቅድ አውጥታ በመተግበር ፈር ቀዳጅ ነች።

የውኃ ደኅንነት ዕቅዷ የውኃ ንጽህናን ከመጠበቅ ባሻገር ነው፡፡ ዋና ትኩረቷ የውኃ ምንጮችን እና ተፋሰሶችን በቀጣይነት መጠበቅ ነው፡፡ ማኅበረሰብ አቀፍ የተፋሰስ ልማት ሥራን በስፋት እየሠራች ያለችው ኢትዮጵያ ይህን ሥራ ከአረንጓዴ አሻራ ጋር አጣምራ የውኃ ምንጮችን ደኅንነት በመጠበቅ ረገድ አበረታች ውጤቶችን እያስመዘገበች ትገኛለች።

እንደ አዲስ አበባ እና አዳማ ባሉ ትላልቅ ከተሞች ውስጥ ያሉ የውኃ ፕሮጀክቶች ከአየር ንብረት ጋር በተያያዙ አደጋዎች ለብክለት እንዳይጋለጡ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው።

በትላልቅ ከተሞች እየተሠሩ ያሉ የኮሪደር ልማት ትሩፋት የሆኑት የወንዝ ዳር ልማቶች ደግሞ የውኃን ደኅንነት ከመጠበቅ አንጻር የራሳቸውን ድርሻ እየተወጡ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ የውኃ ደኅንነት "የሥርዓተ-ፆታ" ጉዳይ ነው፡፡ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍሎች ውኃን ለማግኘት ከፍተኛ ጫና የሚያርፍባቸው ሴቶች እና ልጃገረዶች ይህ ጉዳይ በትኩረት የሚሠራበት ነው።

 

በለሚ ታደሰ