የጥምቀት በዓል በመላው የሀገራችን ክፍሎች በድምቀት ከሚከበሩ የአደባባይ በዓላት አንዱ ነው።
በተለይም በአዲስ አበባ ጃን ሜዳ፣ በጎንደር፣ በምንጃር ሸንኮራ ኢራንቡቲ፣ በባቱ እና በጋምቤላ ባሮ ወንዝ ዳርቻ የሚከበረው የጥምቀት በዓል በርካታ ሰዎች የሚገኙበት ነው።
ለዛሬ በጋምቤላ ባሮ ዳርቻ የሚከበረውን የጥምቀት በዓል በዐይነ ኅሊና ልናስቃኛችሁ ወደድን።
ጥምቀት በባሮ ወንዝ በተለያዩ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ክዋኔዎች የሚከበር ሲሆን የኅብረ-ብሔራዊት ኢትዮጵያ የተለያዩ ባህሎች በአንድነት የሚደምቁበት መድረክም ነው።
የጋምቤላ ጥምቀት ጥር 10 በከተራው በሕብረ ቀለም ተውቦ ይጀምራል።

ከተለያዩ አድባራት የተወጣጡ ታቦታት ከመንበረ ክብራቸው በመውጣት "ወረደ ወልድ" እያሉ ከየአቅጣጫው ወደ ባሮ ወንዝ ሲወርዱ ልዩ ድባብ ይፈጥራሉ።
ታቦታቱ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ የሚወርዱት በምዕመኑ ሃይማኖታዊ መዝሙሮች እና ኅብረ-ዝማሬ እንዲሁም በባህላዊ ጭፈራዎች ታጅበው ነው።
በሞቃታማው የአየር ንብረት የማይበገሩት አገልጋዮች ታቦታቱን ባማረ እና ሞገስ በተሞላበት መልኩ ይሸኟቸዋል።
የከተራ ዕለት ምሽቱ “ምነው ባላለፈ!” በሚያስብል ልክ ድምቀቱ ይማርካል። ታቦታትን በየማደሪያቸው ያስገባው ሕዝብ ገሚሱ በሃይማኖታዊ መዝሙር ገሚሱ ደግሞ በባህላዊ ጭፈራዎች ምሽቱን ያደምቀዋል።

በጉባኤ ላይ የሚሳተፈው ሕዝብ የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ሃይማኖታዊ ትምህርት የሚከታተልበት ሥነ-ሥርዓትም ልዩ ነው።
በተለይ ጥምቀትን ለመጀመሪያ ጊዜ በባሮ ዳርቻ ማሳለፍ ልዩ ስሜት እንደሚፈጥር የሚናገሩ ብዙ ናቸው።

ታቦታቱ ወደየመንበረ ክብራቸው ሲመለሱም ምዕመናኑ በተመሳሳይ መልኩ በዝማሬ እና በምስጋና እንዲሁም በባህላዊ ጭፈራዎች የጋምቤላን ጎዳናዎች ያደምቋቸዋል።
የኢትዮጵያውያን ኅብረት (አንድነት) እና ሕብረ ቀለማት ጎልተው የሚታዩበት የባሮ ዳርቻ የጥምቀት በዓል ውበቱ በቃል ከሚነገረው በላይ ነው።
በየዓመቱ ሃይማኖታዊ ትውፊቱን ጠብቆ በየዓመቱ የሚከበረው ይህ በዓል ዘንድሮም በተመሳሳይ መልኩ ይከናወናል።
በዮናስ በድሉ
#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #Timket #culture