Search

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ አፈጻጸም ከተገመተው በላይ ጠንካራ ሆኖ መገኘቱ ተገለጸ

ማክሰኞ ጥር 12, 2018 207

የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ አፈጻጸም ላይ ወሳኝ ምዕራፍ የሆነውን አራተኛው የጋራ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ግምገማ በስኬት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቁ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና የገንዘብ ሚኒስቴር በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ ኢትዮጵያ በተለዋዋጭ ዓለም አቀፋዊ እና ቀጣናዊ ሁኔታዎች ውስጥ ሆናም፣ የኢኮኖሚ አፈጻጸሟ መጀመሪያ ላይ ከተገመተው በላይ ጠንካራ ሆኖ መገኘቱ በግምገማው እንደተረጋገጠ ገልጸዋል።
የተቀመጡ የልማት ግቦችም ከታቀደው በላይ መሳካታቸውን የጋራ መግለጫው አመላክቷል።
ለዚህ አፈጻጸም እውቅና በመስጠት፣ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ የ261 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ እንዲለቀቅ የፈቀደ ሲሆን፣ ይህም አሁን ባለው ስምምነት መሠረት የሚለቀቀው ጠቅላላ የገንዘብ መጠን ከ2.18 ቢሊዮን ዶላር በላይ መድረሱ ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአሁኑ ወቅት የሚከተሉትን ልዩ ድምር ውጤቶችን እያሳየ ይገኛል፤ በዚህም መሰረት ፦
• ጠንካራ እና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት፣
• ፈጣን የዋጋ ግሽበት ቅናሽ ፣
• የተሻሻለ የበጀት ዲሲፕሊን እና
• የውጭ ምንዛሪ ክምችት በቋሚነት እያደገ መምጣቱን የጋራ መግለጫው አመላክቷል።
እነዚህ ውጤቶች የመደመር መንግሥት ለአጭር ጊዜ መፍትሄዎች ከመገዛት ይልቅ የፖሊሲ አማራጮችን ለመቃኘት፣ ለሀገራዊ የባለቤትነት ስሜት መጎልበት እንዲሁም ለማክሮ ኢኮኖሚው መረጋጋትና ለኢኮኖሚ ማሻሻያው ወጥነት ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነት ያንጸባርቃሉ ተብሏል።
ግልጽ የውጭ ምንዛሪ ጨረታ ስርዓት እና ወደ ገበያ መር ሥርዓት የሚደረገውን ሽግግር ጨምሮ በውጭ ምንዛሪ ገበያ ማሻሻያ ላይ የታዩት ዕድገቶች በራስ መተማመንን በመመለስ የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን ማሻሻል እና የግል ዘርፉን እንቅስቃሴ መደገፍ ያስቻሉ መሆናቸው ተገልጿል።
በበጀት ረገድ፣ በቅርቡ በተደረጉ የታክስ ፖሊሲ እና የታክስ አስተዳደር ማሻሻያዎች በመታገዝ የመንግሥት ገቢ አሰባሰብ ከሚጠበቀው በላይ መሆኑን የጋራ መግለጫው አመላክቷል።
በሌላ በኩል ወጪዎች ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ኢንቨስትመንቶች እና ለማኅበራዊ ጥበቃ ፕሮግራሞች ላይ አተኩረው በጥንቃቄ እንዲመሩ ተደርጓል ተብሏል።
መንግሥት የብድር አመላለስ ዘላቂነትን በተመለከተ የታዩ መሻሻሎችንም በበጎ መልኩ መቀበሉ ተመላክቷል። ይህም በቡድን 20 (G20) የጋራ ማዕቀፍ ሥር የኦፊሴላዊ አበዳሪዎች ኮሚቴ የመግባቢያ ሰነድ መጠናቀቁን የሚያካትት ሲሆን፣ ይህም ኢንቨስትመንትን ለማነቃቃት ወሳኝ እርምጃ መሆኑ ተገልጿል።
የፋይናንስ ዘርፍ ማሻሻያዎች፤ የገንዘብ ፖሊሲን ለማዘመን፣ የባንክ ቁጥጥርን ለማጠናከር እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ገለልተኝነትና አቅም ለማሳደግ የሚያስቸሉ ተግባራት መቀጠላቸውም ተጠቁሟል።
የመደመር መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋቱን ወደ ሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ወደ ግል ኢንቨስትመንት እና ወደ ገቢ ዕድገት ለመለወጥ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ፣ እንዲሁም ሁሉንም አሳታፊ እና ዘላቂ ዕድገትን የሚደግፉ ማሻሻያዎችን ይበልጥ እንደሚያጠናክር በመግለጫው ተመላክቷል።