በአዋጅ ቁጥር 487/2014 የተመሰረተው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ (Ethiopian Investment Holdings - EIH) የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ጉልህ ውጤት ነው።
ተቋሙ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ የሚገኝ ስትራቴጂካዊ ተቋም ሆኗል።
የኢኮኖሚው ሞተር እና የሪፎርም መሪ ሆልዲንግሱ የተመሰረተው የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በዘመናዊ መንገድ ለማስተዳደር እና የሀገርን ሀብት ለትውልድ እንዲተርፍ ለማድረግ ነው።
በአሁኑ ወቅት የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ሊበራላይዜሽን (Liberalization) ሂደት በመምራት እንደ "ኢኮኖሚ ሞተር" እያገለገለ ይገኛል። ቀደም ሲል በመንግሥት እጅ ብቻ የነበሩ ድርጅቶችን ወደ ግል ዘርፉና ወደ ካፒታል ገበያው ለማሸጋገርም እንደ ዋና ድልድይ ሆኖ እየሰራ ነው።
በአፍሪካ ግንባር ቀደም የሉዓላዊ ፈንድ EIH በአፍሪካ ካሉ ግዙፍ ሉዓላዊ ፈንዶች አንዱ ሲሆን፣ ከ27 በላይ ትላልቅ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በስሩ ያስተዳድራል። ከእነዚህም መካከል፦
· የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኢትዮ ቴሌኮም፤
· የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፤
· የኢትዮጵያ መርከብና ሎጅስቲክስ አገልግሎት፤
· የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የስኳር ፋብሪካዎችና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተጠቃሽ ናቸው።
የእነዚህ ድርጅቶች አጠቃላይ የሀብት መጠን ተቋሙን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ያደርገዋል። ‘አፍሪካን ካፒታል ማርኬት ኒውስ’ እንደጠቀሰው፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በአሁኑ ወቅት ከ38 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ሀብት ያስተዳድራል።
የካፒታል ገበያው ፈር ቀዳጅ ተቋሙ በቅርቡ ሥራ ለጀመረው የኢትዮጵያ ሰነደ መዓለ ንዋዮች ገበያ (ESX) መሳካት ቁልፍ ሚና አለው። በገበያው ውስጥ የ25 በመቶ ድርሻ በመያዝ ግንባር ቀደም መሥራች መሆኑ ይታወቃል።
የኢትዮ ቴሌኮምን 10 በመቶ ድርሻ ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ ለመሸጥ የተጀመረው ሂደትም፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሕዝብ ባለድርሻነት እንዲረጋገጥ ተቋሙ እየሰራ መሆኑን ያሳያል።
ዓለም አቀፍ ትስስር እና ኢንቨስትመንት ፈንዱ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን (FDI) በመሳብ ረገድ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል።
ከተለያዩ የባሕረ ሰላጤው ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በግብርና፣ በኢነርጂ እና በሪል እስቴት ዘርፎች የጋራ ኢንቨስትመንት ስምምነቶችን ተፈራርሟል።
በተጨማሪም የዓለም አቀፍ የሉዓላዊ ፈንዶች መድረክ (IFSWF) አባል በመሆን አሠራሩን ግልጽና ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ እያደረገ ነው።
ከኪሳራ ወደ ትርፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ እንደገለጹት፣ ቀደም ሲል እስከ 99 በመቶ ኪሳራ ውስጥ የነበሩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ አማካኝነት ወደ አትራፊነት ተሸጋግረዋል። በተለይም እንደ ስኳር ፋብሪካዎች ያሉ ተቋማትን ከኪሳራ በማውጣት የልማት ደጋፊ እንዲሆኑ እያደረገ ይገኛል።
ግልጽነትና ተጠያቂነት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በሚያስተዳድራቸው ድርጅቶች ውስጥ የሙስና እና ብልሹ አሠራሮችን ለመከላከል የሚያስችል ዘመናዊ አሠራር ዘርግቷል።
ለዚህም ሲባል የህዝብ አስተያየቶችን እና ጥቆማዎችን በቀላሉና በምስጢር መቀበል የሚያስችል ድረ-ገጽ እና መተግበሪያ ይፋ አድርጎ ወደ ሥራ ገብቷል።
#Ethiopia #EIH #EconomyReform #Investment #የኢትዮጵያኢንቨስትመንትሆልዲንግስ