Search

ለሁሉን አቀፍ እድገት አዲስ ምዕራፍ የከፈተው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ

ማክሰኞ ጥር 19, 2018 109

ኢትዮጵያ የተገበረችው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በሀገራችን የኢኮኖሚ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው።

ማሻሻያው በተለይም የዋጋ ግሽበትን በመቆጣጠር፣ የውጭ ንግድ ሚዛንን በማስተካከልና ለግሉ ዘርፍ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ እድገት እንዲመዘገብ አስችሏል።

በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ ዘላቂና ጤናማ የኢኮኖሚ ማዕቀፍ ለመገንባት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይገልፃሉ።

በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የኢኮኖሚ ተመራማሪ የሆኑት ብርሐኑ ዓለሙ (/) ማሻሻያው በግሉ ዘርፍ ለሚመራና ሁሉን አቀፍ ለሆነ የኢኮኖሚ እድገት መሰረት የሚጥል መሆኑን ተናግረዋል።

መንግሥት ፖሊሲውን ተግባራዊ ከማድረጉ በፊት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጉንም ምሁሩ ጠቅሰዋል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዮሐንስ በቀለ በበኩላቸው፤ የማሻሻያው ስኬት በባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ይናገራሉ።

በተለይም በአሁኑ ወቅት አብዛኛው ነጋዴ ምርትን ከውጭ አምጥቶ በመቸርቸር ላይ ብቻ ትኩረት ማድረጉን ጠቅሰው፤ አዲሱ ፖሊሲ ግን የአገር ውስጥ አምራችነትን የሚያበረታታ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ባለሙያዎቹ አክለውም፤ ህብረተሰቡ ለፖሊሲው ትግበራ ተባባሪ መሆን እንዳለበት ገልጸው፤ ይሁን እንጂ በማሻሻያው የትግበራ ሂደት ውስጥ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫናዎችን ለመቀነስ መንግሥት የአጭር ጊዜ መፍትሔዎችንና የድጋፍ ማዕቀፎችን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል።

ይህ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታን በመፍጠር የሀገሪቱን የንግድ ተወዳዳሪነት እንደሚያሳድግም ነው የገለፁት።

በንፍታሌም እንግዳወርቅ