ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ በምክር ቤት ባደረጉት ማብራሪያ፣ "ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ በኢንዱስትሪው ዘርፍ አመርቂ ለውጥ መመዝገቡን ገልጸዋል።
ንቅናቄው ሲጀመር ከ47 በመቶ ያልበለጠ የነበረው የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም፣ በሦስት ዓመታት ውስጥ ብቻ ወደ 66.3 በመቶ ከፍ ማለቱ የሀገሪቱን የማምረት አቅም ጥንካሬ የሚያሳይ ሆኗል።
በተለይም ባለፉት ስድስት ወራት የኢንዱስትሪዎች የኢነርጂ አጠቃቀም በ16 በመቶ ማደጉ፣ ፋብሪካዎቻችን በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ እየገቡ መሆናቸውን ያረጋገጠ ድንቅ ስኬት ነው።
ይህ ብሔራዊ ንቅናቄ ለሀገር ውስጥ ምርት ትኩረት በመስጠቱ ብቻ ቀደም ሲል 3.4 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ይደረግባቸው የነበሩ የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ይህ ውጤት የውጭ ምንዛሬን ከማዳን ባለፈ ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፣ ከዘርፉ የሚገኘው የወጪ ንግድ ገቢም የበጀት ዓመቱ ሲጠናቀቅ በእጥፍ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል።
በአጠቃላይ በኢንዱስትሪው ዘርፍ እየታየ ያለው ይህ መነቃቃት፣ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም የበለፀገችና የምትመገብ ሀገር ለመሆን ለጀመረችው ጉዞ ትልቅ ዋስትና ሆኗል።