ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመደመር መንግሥት የሀገሪቱን የዕዳ ጫና በመቀነስ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡን ገለጹ።
ኢትዮጵያ ከለውጡ በፊት በከባድ የዕዳ ጫና ውስጥ እንደነበረች ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በተለይም ቀደም ሲል ይወሰድ የነበረው የንግድ ብድር ለሀገሪቱ ትልቅ ፈተና እንደነበር ጠቁመዋል።
ይህ ዓይነቱ ብድር የሀገሪቱን የፋይናንስ አቅም በማዳከሙ፣ አበዳሪዎች ተጨማሪ ብድር ለመስጠት ተጠራጥረው እንደነበርም አብራርተዋል። የሌብነት መስፋፋት እና የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ድክመት ችግሩን ይበልጥ አወሳስቦት እንደነበርም አንስተዋል።
ይሁን እንጂ ከለውጡ በኋላ ኢትዮጵያ አንድም የንግድ ብድር አለመውሰዷን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ይህ እርምጃ ምስጋና የሚገባው ጠንካራ የፖሊሲ አቅጣጫ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተውበታል።
በተጨማሪም ቀድሞ የተወሰዱ የንግድ ብድሮችን ወደ መደበኛ ብድር ለመቀየር የተደረገው አድካሚ ድርድር ስኬታማ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያ የብድር ሁኔታ እጅግ አስተማማኝ ደረጃ ላይ እንደሚደርስም አረጋግጠዋል።
በለሚ ታደሰ
ኢቢሲ ዶትስትሪም - የመረጃዎ ድልድይ! ሙሉውን ዘገባ እና ዝርዝር መረጃዎችን በኢቢሲ ዶትስትሪም ዲጂታል አማራጮች ይከታተሉ።