የሀሰተኛ መረጃዎችን በማዘጋጀትና በማሰራጨት በኩል የተለያዩ አካላት ተሳታፊዎች ናቸው፤ ከነሂህም ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሱት፦
• ግለሰቦች- አንዳንድ ግለሰቦች ሃሰተኛ መረጃ አቀነባብረው በማስራጨት ትኩረትን ለማግኘት ይሞክራሉ:: በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚሳተፉ ግለሰቦች እና በተጠቃሚዎች መካከል ልዩነት የሚፈጥር እንዲሁም ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ መረጃዎችን በመልቀቅ ትኩረት ለማግኘት የሚጥሩ ግለሰቦች ናቸው።
• ለገንዘብ የሚሰሩ አካላት- እነዚህ ካላት በዋናነት ለሚያዘጋጁት ይዘት በርካታ ተጠቃሚ በማፍራት በሂደት ማስታወቂያዎችን እና ስፖንሰር በመሳብ ትርፍ ማግኘት የሚፈልጉ ናቸው። በዚህ ስራ የሚሳተፉ አካላት የሚያዘጋጁት መረጃ ዋና ዓላማ የታዳሚ ቁጥር ማስገኘት እስከሆነ ድረስ ወደ ማህበራዊ ሚዲያው የሚለቀቀው መረጃ ችግር ያለበት እና ሰዎችን የሚያሳስት ይሆናል። ሀሰተኛ መረጃን በማዘጋጀት የተጠቃሚ ቁጥር በመጨመር ከሚገኘው ገንዘብ ለመጠቀም ቀንና ለሊት የሚተጉ የሀሰተኛ መረጃ ፋብሪካዎች በርካታ ናቸው።
• አክቲቪስቶች፦ የተለያየ ዓላማን አንግበው በየጎራው ተሰልፈው በታዳሚያን አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር የሚሰሩ ናቸው:: አነዚህ አካላት በርካታ ቁጥር ያለው የማህበራዊ ሚዲያ ተከታይ ያላቸው ከመሆኑ አንጻር በተለያዩ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ የሚያስተላልፉት የተዛባ መረጃ የሚፈጥረው ተጽዕኖ ቀላል እንዳልሆነ መግለጽ ይቻላል:: አንዳንድ ተራ መረጃዎችንም ጭምር በማጣፈጥ እና እንደ ትልቅ አጀንዳ መልሶ በመቅረፅ ተቀባብለው አጀንዳ የማድረግ አዝማሚያዎችም አሉ።
• ፖለቲከኞች - የተለየ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች ሀሰተኛ መረጃ ከማሰራጨት አንጻር ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል:: የዘመኑ የፖለቲካ ትግል በፊት ለፊት የመድረክ ክርክር ብቻ ሳይወሰን ዘመኑ ያፈራውን የስነ-ተግባቦት ዘዴ በመጠቀም ጭምር የሚካሄድ ነው:: ፖለቲከኞች በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሀሳባቸውን እየጻፉ በቀላሉ ለተከታዮቻቸው እና ለማህበራዊ ሚዲያ ታዳሚያን ያሥተላልፋሉ።