በኢትዮጵያ እና በቱርክዬ መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ ቢያንስ ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር እና ከዚያም በላይ ማደግ እንዳለበት ከቱርክዬ ፕሬዚዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን ጋር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የገለጹት በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ከሚገኙት የቱርክዬ ፕሬዚዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን ጋር በሰጡት የጋራ መግለጫ ነው።
በመግለጫቸውም፥ የሁለቱ ሀገራት የንግድ ልውውጥ ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንዲሸጋገር እና የቱርክዬ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት በማድረግ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው የአፍሪካ ገበያ እንዲሠሩ ከፕሬዚዳንት ኤርዶዋን ጋር መምከራቸውን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ የ10.2 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት እንደምትጠብቅ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ይህን የኢኮኖሚ ዕድል ለጋራ ዕድገት መጠቀም ወሳኝ መሆኑን አስምረውበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፕሬዚዳንት ኤርዶዋንን፥ የሰው ዘር እና የቡና መገኛ ወደሆነችው፤ በቅኝ ወዳልተገዛችው እና ከፍተኛ ክብር፣ ኩራት እንዲሁም የማደግ ተስፋ ወዳላት ወደ ኢትዮጵያ "እንኳን ደኅና መጡ" ብለዋቸዋል።
በተጨማሪም ፕሬዚዳንት ኤርዶዋን በደቡብ አፍሪካ በነበረው የቡድን 20 ስብሰባ ወቅት የተደረገላቸውን ግብዣ አክብረው ኢትዮጵያን በመጎብኘታቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በለሚ ታደሰ
#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #PMAbiy #RecepTayyipErdoğan #Turkiye #Diplomacy