Search

የኤምሬትስ አዲሱ ንጉሥ፦ ማክስ ዶውማን

እሑድ መጋቢት 06, 2018 56

ዓመቱን ሙሉ ፊቱ ተቋጥሮ በጭንቀት ስታዩት የነበረው ሚኬል አርቴታ ድንገት እንደ እንቦሳ ጥጃ ሲፈነጥዝ ያያችሁት፣ 90 ደቂቃ በፍርሀት የተዋጠው ኤምሬትስ በአንድ እግሩ እንዲቆም የሆነው ደግሞም የዋንጫው ቀጥተኛ እና ተፎካካሪው አሠልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ሁለት ቀን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሁለት የሚጋጩ ሐሳቦችን ለመሰንዘሩ ምክንያቱ ባለተሰጥኦው ማክስ ዶውማን ነው። 

አርሰናል 22 ዓመታት በፊት ያለ ምንም ሽንፈት የፕሪሚየር ሊጉን የወርቅ ዋንጫ ሲያነሳ እሱ በዚህ ምድር አልነበረም። የአርሰናልን 49 ተከታታይ ጨዋታዎች ያለመሸነፍ ታሪክ የሚያውቀው የክለቡ ታማኝ ደጋፊ ከሆኑት ቤተሰቦቹ በሰማው ትረካ ብቻ ነው።

እሱ የሚውያቀው አርሰናል ውጤት የከዳውን ለዋንጫ ሳይሆን ለሻምፒንስ ሊግ ተሳትፎ በየዓመቱ የሚታገለውን እና ፈተና የበዛበትን ቢሆንም በልቡ ውስጥ የነበረው የመድፈኞቹ ፍቅር ግን ከታሪክ ማኅደር የጠነከረ እንደነበር አሁን እያደረገ ያለውን ነገር መመልከት በቂ ይሆናል።

የዶውማን ታሪክ የሚጀምረው በለንደን ዳርቻ፣ የቶተንሃም እና የዌስትሃም ደጋፊዎች በሚበዙባት ቢሊሪኬይ ከተማ ነው። ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ካላቸው ቤተሰቦች የተገኘው ማክስ ዶውማን፣ እግር ኳስን የተማረው ከቤተሰቦቹ ነው።

አባቱ በታችኛው ሊግ ለሚገኘው ቢሊሪኬይ ክለብ ከተጫዋችነት እስከ አሠልጣኝነት ሲያገለግሉ፣ አያቱ ደግሞ የዚሁ ቡድን ግብ ጠባቂ ነበሩ። እናቱ በክለቡ ሱቅ ውስጥ በመሥራት፣ ወንድም እና እህቶቹም በክለቡ አቅራቢያ በሚገኝ መጠጥ ቤት በመቀጠር ለኑሮ ሲታገሉ፣ ማክስ ግን በዚያው የእግር ኳስ ድባብ ውስጥ የወደፊት የዓለም ኮከብነቱን እያሳየ አደገ። 

ገና በአራት ዓመቱ ከኳስ ጋር የተዋወቀው ይሄ ታዳጊ፣ በስድስት ዓመቱ የበርካታ ክለቦችን ትኩረት ቢስብም ምርጫው ግን አንድ ብቻ ነበር። ሀሉም ቤተሰቡ ለአርሰናል ያላቸው ጥልቅ ፍቅር፣ ታዳጊውን ከአስር ዓመት በፊት ወደ መድፈኞቹ አካዳሚ እንዲያመራ አደረገው።

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አርሰናል ሊድስን 5 0 ባሸነፈበት ጨዋታ ለመጀመርያ ጊዜ የተሰለፈው ማክስ ዶውማን ትላንት ምሽት ሌላኛውን ትልቅ ታሪክ ሠርቷል። በአንድ ቀን ለዚያውም 16 ደቂቃ ውስት ሁለት የገዘፉ ታሪኮችን መሥራት የተቻለው 16 ዓመቱ ማክስ ዶውማን ብቻ ነው።

30 ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አርሰናል ከተከታዩ ሲቲ ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማስፋት እና ይበልጥ ወደ ዋንጫ ለመጠጋት ኤቨርተንን ግዴታ ማሸነፍ ነበረበት።

ግን እንዴት? መድፈኞቹ ሦስት ነጥብ ለማግኝት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ካቴናውን የኤቨርተን የተከላካይ ክፍል ማለፍ አልቻሉ። የሚፈለገውን ነጥብ ለማግኘት አንድ 16 ዓመት ወጣት ወደ ሜዳ መግባት ነበረበት። 74ኛው ደቂቃ ላይ ማክስ ዶውማን ዓመቱን ሙሉ ያለ ዕረፍት የተጫወተውን ማርቲን ዙቢሜንዲን ተክቶ ወደ ሜዳ ገባ። አብዝቶ ጥንቃቄን የሚመርጠው ሚኬል አርቴታ በዚህ ፈታኝ ሰዓት ምንም ልምድ ለሌለው ወጣት ዕድል ይሰጣል ተብሎ ባይጠበቅም አደረገው።

ሜዳ ውስጥ በቆየባቸው 16 ዲቃዎች ሜዳውን እንደፈለገ ፈነጨበት ኳስ ሲይዝ ያምርበታል፣ ሁለት ሦስት ተጫዋቾችን ማለፉንም እንደዚያው ይችልበታል። ዶውማን ዮኬሬስ ላስቆጠረው ግብ መገኘት ምከንያት ከመሆኑ በተጨማሪ በባከነ ሰዓት በቄንጠኛ እግሮቹ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ሁለት የኤቨርተን ተጫዋቾችን በማለፍ ግብ አስቆጥሮ ኤምሬትስ በአንድ እግሩ እዲቆም አደረገ። ዶውማን በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ ግብ ያስቆጠረ በዕድሜ ትንሾ ኮከብ ሲሆን ምን አልባትም አርሰናል ተሳክቶለት የሊጉን ዋንጫ 22 ዓት በኋላ ካነሳ ለለዋንጫው መገኘት እንደ ምከንያት ከሚቆጠሩ ጉዳዮች አንደኛውን የሚታወስ ምሽት ያሳለፈበትም ሆኗል።

ትምህር ቤት ሲሄድ እኩዮቹ የሚገረሙበት ዶውማን ዕድሜው አይደለም በዓለም ቁጥር አንድ በሆነው ሊግ ልዩነት ለመፍጠር ይቅርና 2 ደረጃ ትምህርት ቤት ፈተናዎችን እንኳን ለመጋፈጥ ገና ቢሆንም ከቤተሰቦቹ የወረሰው የአርሰናል ፍቅር እና የታታሪነት መንፈስ፣ የክለቡ ብቻ ሳይሆን የመጪው ዘመን የእንግሊዝ እግር ኳስ ተስፋ አድርጎታል።

የቀድሞው የቼልሲ ተከላካይ ጆን ቴሪ በተጫዋችነት ዘመኔ ከሊዮኔል ሜሲ ውጪ ኳስን አቅልሎ የሚጫወት እና በዚህል ልክ ተጫዋቾችን የሚያልፍ ወጣት አላየሁም ብሎ የመሰከረለት ዶውማን አርሰናል ከሁለት አስርት ዓመታት በኋላ የሊጉን ዋንጫ ካነሳ፣ ይቺ የዶውማን 16 ደቂቃ አስማታዊ ምሽት እንደ ዋነኛ ታሪክ ተጠቃሽ ሆና ትኖራለች።

በአንተነህ ሲሳይ