Search

የኢትዮጵያን ግብርና ለማዘመን የሚረዱ በ2.3 ቢሊዮን ብር የተገዙ የሜካናይዜሽን መሣሪያዎች ለክልሎች ተሰራጩ

እሑድ መጋቢት 13, 2018 68

የግብርና ሚኒስቴር የኢትዮጵያን የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ከባህላዊ አሰራር ወደ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ሥርዓት ለማሸጋገር እና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ፣ በ2.32 ቢሊዮን ብር የተገዙ የሜካናይዜሽን መሣሪያዎችን፣ ተሽከርካሪዎችንና የቴክኖሎጂ ቁሳቁሶችን ለክልሎች አስረክቧል።
የግብርና ሚኒስትሩ አቶ አዲሱ አረጋ መሣሪያዎቹን ለክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊዎች ባስረከቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ ይህ ሰፊ ድጋፍ አርሶ አደሩን ከልማዳዊ አሰራር በማውጣት ወደ ዘመናዊ የግብርና ሥርዓት ለማሸጋገር የሚደረገውን ሀገራዊ ጥረት በእጅጉ የሚያግዝ ነው።
ለክልሎቹ የተሰራጩት ከ1 ሺህ 990 በላይ ትራክተሮች፣ የሩዝ ማቀነባበሪያ ማሽኖች፣ የውሃ መሳቢያ ፓምፖች፣ የመስክ ተሽከርካሪዎች፣ ሞተር ሳይክሎች፣ የጫጩት ማስፈልፈያ መሣሪያዎችና ሌሎችም የቴክኖሎጂ ውጤቶች የምርት ጥራትን ከመጠበቅ ባለፈ የአርሶ አደሩን ድካምና ጊዜ በእጅጉ የሚቀንሱ ናቸው።
ሚኒስትሩ አክለውም ሜካናይዜሽን ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ የምርት ጥራትንና የገበያ ተወዳዳሪነትን በማሻሻል የአርሶ አደሩን ኑሮ በዘላቂነት እንደሚለውጥ ገልጸዋል፡፡
መሣሪያዎቹም ከደቡብ ኮሪያ መንግሥት፣ ከምግብ ሥርዓት ማጠናከሪያ፣ ከዘላቂ መሬት አያያዝ፣ ከበረሃ አንበጣ መከላከል፣ ከልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራሞች እና ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ መገዛታቸውን ጠቁመዋል።
ይህ ሰፊ የቴክኖሎጂ ስርጭት በዋናነት የሀገሪቱን የምግብ ዋስትናና ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የሚደረገው የተቀናጀ ሀገራዊ ስራ አካል መሆኑ ተገልጿል።
በወንድማገኝ ሀይሉ