የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ድኅነት ሲል በመስቀል ላይ የዋለበትን "ዕለተ ስቅለት" በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት እያሰቡት ይውላሉ።
የቤተክርስቲያኗ ሊቃውንትና አባቶች እንደሚያስተምሩት፤ ይህ ዕለት አምላክ በመስቀል ላይ በከፈለው መሥዋዕትነት የሰውን ልጅ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን ያሸጋገረበት የፍጹም ፍቅር መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል።
በዕለቱ የሚከናወነው ሥርዓተ አምልኮ ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ድረስ በ12 የጸሎት ሰዓታት የተከፋፈለ ነው።
በእነዚህ ሰዓታት ክርስቶስ በጲላጦስ አደባባይ መቆሙ፣ መገረፉ፣ በመስቀል ላይ መቸንከሩ እና ነፍሱን ከሥጋው የመለየቱ ምስጢር በሰፊው ይዘከራል።
ሊቃውንቱ እንደሚገልጹት፤ በስቅለት ዕለት የሚከናወኑት እንደ ዕጣን አለማጠን እና የደወል ድምፅ አለማሰማት ያሉ ሥርዓቶች ኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበለውን መከራ እና እንግልት የሚዘክሩ ተምሳሌታዊ ትርጉሞች አሏቸው።
ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት እስከ ገዳማት የሚከናወነው ሥርዓተ አምልኮ በሰዓታት የተከፋፈለ ሲሆን፤ ከጠዋቱ 12 ሰዓት (ነግህ) ጀምሮ ክርስቶስ በጲላጦስ አደባባይ የቆመበት፣ በ6 ሰዓት (ቀትር) የተሰቀለበት እና በ9 ሰዓት (ተሰዓተ ሰዓት) ቅዱስ ነፍሱን ከሥጋው የለየበት ታላቅ ምስጢር በምእመናን ዘንድ በዝምታ እና በታላቅ መንፈሳዊ ሐዘን ይታሰባል።
የዕለቱ ልዩ መገለጫ የሆነው እና በአራቱ ማዕዘናት የሚከናወነው የ400 ጊዜያት ስግደት፤ ክርስቶስ በምድር ላይ የቆየባቸውን 400 ወራት (33 ዓመት ከ3 ወራት) ታሳቢ ያደረገ መሆኑ ይነገራል።
ይህም ቤዛነቱ ዓለም አቀፋዊ መሆኑን የሚያመለክት እንደሆነ ቤተክርስቲያኗ ታስተምራለች። ከዚህም በተጨማሪ ምእመናን "አክፍሎ" በመባል የሚታወቀውን እና ከሐሙስ ምሽት ጀምሮ እስከ ትንሣኤ ሌሊት የሚቆይ ጥብቅ ጾም በመጾም መከራውን ያስባሉ።
በቤተክርስቲያኗ ሥርዓት መሠረት በዚህ የሕማማት ሳምንት እንደ ፍትሐትና ጥምቀት ያሉ መደበኛ አገልግሎቶች የማይከናወኑ ሲሆን፤ ትኩረቱ ሁሉ በመስቀሉ መሥዋዕትነት ላይ ብቻ እንዲሆን ይደረጋል።
የሃይማኖት አባቶች ዕለቱ የጥል ግድግዳ ፈርሶ ሰላም የወረደበት መሆኑን በመጥቀስ፤ መላው ማኅበረሰብ ቀኑን በሰላም፣ በይቅርታ እና በታላቅ መንፈሳዊ ትሕትና ሊያሳልፈው እንደሚገባ ያስተምራሉ።
በለሚ ታደሰ