Search

ለኢትዮጵያ አሸናፊነት የተሰጠ ምስክርነት፡ የዴሞክራሲ ጉዞ እና የአፍሪካ አዲስ ተምሳሌት

ረቡዕ ግንቦት 26, 2018 42

ግንቦት 24 ቀን የተካሄደው 7ኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ በሀገራችን የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አዲስ ብሩህ ምዕራፍ የከፈተ ነው።

ይህ ታሪካዊ ክስተት ኢትዮጵያ በውስብስብ ፈተናዎች ውስጥም ሆና የላቀ ዴሞክራሲያዊ ድል መቀናጀት እንደሚቻል በተግባር ያሳየችበት ትልቅ የታሪክ ማረጋገጫ ሆኗል።

ምርጫውን ተከትሎ የአፍሪካ ኅብረት፣ የኢጋድ፣ የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት፣ ካናዳ፣ ኖርዌይ እና ስዊዘርላንድ ያወጧቸው ይፋዊ መግለጫዎች ይህንን እውነት በጉልህ ይመሰክራሉ።

እነዚህ ዓለም አቀፍ ምስክርነቶች የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ሽግግር መልክ የሚያሳዩ ብቻ ሳይሆኑ፣ ሀገራችን በራሷ መንገድ ለመላው የአፍሪካ አህጉር ተምሳሌት ሊሆን የሚችል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እየገነባች መሆኗን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያበሰሩ ናቸው።

ሀገር በቀል ፈጠራ እና የሉዓላዊነት ማረጋገጫ ኢትዮጵያ የራሷን ዕድል በራሷ የመወሰን ሉዓላዊ መብቷን በተግባር ያሳየችበት ይህ ምርጫ፣ በቴክኖሎጂያዊ እመርታዎቹም ጭምር አዲስ የላቀ ደረጃን ያስመዘገበ ነበር።

የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ልዑክ መሪ እና የቀድሞዋ የዩጋንዳ ምክትል ፕሬዚዳንት ስፔሲዮዛ ዋንዲራ ካዚብዌ (/) በሰጡት ምስክርነት፣ ምርጫው በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ውስጥ ታላቅ ምዕራፍ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በተለይም "ምርጫዬ" የተሰኘውን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ አቅም የበለጸገ ዲጂታል የመራጮች ምዝገባ ሥርዓት እና የጂአይኤስ (GIS) ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ ማዋሏ፣ ሀገራችን ያላትን ተቋማዊ ብስለት ያሳየ ነው።

መሪዋ አክለውም፣ ይህ በራስ አቅም የመጠቀም ስኬት ለምርጫው አካታችነት፣ ግልጽነት እና ውጤታማነት የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከተ መሆኑን ገልጸው፣ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ሊከተሉት የሚገባ ታላቅ ተሞክሮ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

ይህ ስኬት በተለይም የኢትዮጵያ ወጣቶች በዕውቀት እና በቴክኖሎጂ ዘርፍ ሀገራቸውን ወደ አዲስ ከፍታ ለማሸጋገር ያላቸውን ብቃት ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ኩራት ነው።

የሕዝቡ ጽኑ ተነሳሽነት፣ የሰላም ፍላጎት እና ሕብረት የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እና ለሀገራዊ አንድነት ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነት እና የላቀ ተነሳሽነት በተግባር ያሳየበት ልዩ የምርጫ ዕለት ነበር።

የአፍሪካ ኅብረት ታዛቢ ቡድን መሪ እና የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እንደመሰከሩት፣ የመራጮች ድምፅ አሰጣጥ ሂደት እጅግ ሰላማዊ እና የተረጋጋ ነበር።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ያሳየው ታላቅ የትዕግሥት እና የሥልጣኔ ሰልፍ፣ ፖለቲካዊ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለውን ጽኑ ዝግጁነት ያሳያል።

የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ቡድንም ማኅበረሰቡ ከማለዳው 1100 ሰዓት ጀምሮ በምርጫ ጣቢያዎች በሰላም ተሰልፎ ከመጠበቁም በላይ፣ እርስ በእርሱ ቡና እና ቆሎ በመጋበዝ ያሳየውን ልዩ ባህላዊ መስተንግዶ እና አብሮነት በከፍተኛ አክብሮት አድንቋል።

ይህ ተግባር የኢትዮጵያ ሕዝብ ከግጭት ይልቅ ለውይይት፣ ለፍቅር እና ለሰላም ያለውን ጥልቅ ፍላጎትና ብስለት ለዓለም ማኅበረሰብ በሚገባ ያስመሰከረበት ታላቅ አጋጣሚ ሆኗል።

የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዕውቅና እና የአህጉራዊ መፍትሔ ፋና ወጊነት

የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት፣ ካናዳ፣ ኖርዌይ እና ስዊዘርላንድ በጋራ ባወጡት መግለጫ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ሂደት በደስታ የተቀበሉት መሆኑን ገልጸዋል።

ቡድኑ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለእጩዎች እና ለሲቪል ማኅበራት ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሙሉ ዕውቅና ሰጥቷል።

ምንም እንኳን በጸጥታ ፈተናዎች ምክንያት በጥቂት የምርጫ ክልሎች ድምጽ የመስጠት ሂደት ለጊዜው ቢዘገይም፣ ሁኔታዎች ሲፈቅዱ ቀሪ ምርጫዎችን ለማካሄድ ቦርዱ የገባውን ቃል ሁሉም ወገኖች በአዎንታዊነት ተቀብለውታል።

የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ባስተላለፉት ጠንካራ እና አነቃቂ መልዕክት፣ ታላቋ እና በታሪኳ ቅኝ ተገዝታ የማታውቀው የነፃነት ተምሳሌቷ ኢትዮጵያ፣ ይህንን ታሪካዊ ስኬት በመጠቀም በሕዝቦቿ መካከል ያለውን ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ውይይት ይበልጥ ማጠናከር እንዳለባት አሳስበዋል።

ኢትዮጵያውያን ሁሉንም ወገኖች በማሳተፍ "ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ" በሚለው ታላቅ መርህ መሠረት፣ ፈተናዎችን በውይይት እና በመግባባት በመፍታት ለአህጉሪቱ መሪ እና ተምሳሌት መሆን እንደሚገባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

ይህ ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ልምምድ ማሳያ ብቻ ሳይሆን፣ የተረጋጋች እና በኢኮኖሚ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት የተጣለ ጠንካራ መሠረት ነው።

ከምርጫው ማግስት የሚጠበቀው ትልቁ ተግባር፣ ልዩነቶችን ወደ ጠረጴዛ በማምጣት በብሔራዊ መግባባት ላይ የተመሠረተች እና የዜጎቿን ብልጽግና ያረጋገጠች ጠንካራ ሀገርን በጋራ መገንባት ነው።

በአጠቃላይ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት በጋራ ሆነው የሀገራችንን ታላቅነት፣ ሉዓላዊነት እና የዴሞክራሲ አሸናፊነት በተግባር ያረጋገጡበት ብሩህ ታሪካዊ ድል ሆኖ ይመዘገባል።

በለሚ ታደሰ