የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የድምፅ የመስጠት እና የቆጠራ ሂደት በስኬት እና በሰላም መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል አስራት ደኔሮ ገለጹ።
ዋና አዛዡ ለተመዘገበው ስኬት መላው ሕዝብ፣ ምርጫ አስፈጻሚዎች እና የፀጥታ አካላት በጋራ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ገልጸው፣ የተገኘውን ድል ማፅናት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የፀጥታ አካሉ ወገንተኝነት ለሕገ-መንግሥቱ እና ሕገ-መንግሥቱን መሠረት አድርገው ለሚወጡ ሕጎች ብቻ መሆኑን የጠቀሱት ሌተናል ጄኔራል አስራት፣ መንግሥት ሥልጣን መያዝ የሚቻለው በምርጫ ብቻ መሆኑ በሕግ የተደነገገ መሆኑን አንሥተዋል።
ዜጎች ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በነቂስ ወጥተው መሪዎቻቸውን መምረጣቸውን አስታውሰው፣ ሕዝቡ በተለይም በድምፅ መስጫው ዕለት ያሳየው ትዕግሥት እና የነቃ ተሳትፎ የሚደነቅ መሆኑንም አክለዋል።
የምርጫውን ሂደት ለማደናቀፍ በፀረ-ሰላም ኃይሎች የታሰቡ የተለያዩ ሴራዎች በሕዝብ እና በፀጥታ አካላት ጥምረት መክሸፋቸውን ዋና አዛዡ ጠቁመዋል።
በመሆኑም የሥልጣን ባለቤት የሆነውን የሕዝብ ድምፅ ማክበር ከሁሉም ወገን እንደሚጠበቅ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በአሁኑ ወቅት የምርጫው ሦስተኛ ምዕራፍ መቀጠሉን የገለጹት ሌተናል ጄኔራል አስራት ደኔሮ፣ የምርጫ ውጤት ተገልጾ መንግሥት እስኪመሠረት ድረስ ባለው ሂደትም የሕዝቡ የነቃ ተሳትፎ እና የፀጥታ ተቋማት ዝግጁነት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል።
የምርጫውን ደኅንነት በብቃት ላረጋገጡት ለሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት፣ ለፌዴራል ፖሊስ፣ ለአዲስ አበባ ፖሊስ እንዲሁም ለሌሎች የፀጥታ እና የሰላም መዋቅሮች በምርጫ ኮማንድ ፖስቱ ስም ላቅ ያለ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።