Search

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የታየው የዜጎች ተሳትፎ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ዕድገት ያመላከተ ነው - ምሁራን

ዓርብ ግንቦት 28, 2018 71

ግንቦት 24 የተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በኢትዮጵያ ታሪክ ከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ የታየበት ሆኖ አልፏል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ዜጋ እና ሥነ ምግባር መምህሩ አቶ ብሩክ ደስታ በምርጫው የታየው ጠንካራ የዜጎች የፖለቲካ ተሳትፎ በሀገራችን የፖለቲካ ምህዳር እየሰፋ መምጣቱን እና የሕዝቡ የዴሞክራሲ ግንዛቤ ማደጉን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ አስተዳደር መምህር እና የፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አየለ አዳቶ በበኩላቸው፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቅድመ ምርጫ ወቅት ያደረጉት ስልጡን የሐሳብ ክርክር ዜጎች በንቃት ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እንዲወጡ በማነሳሳት በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል።

በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ አሸናፊ የሚሆነው በሕዝብ አመኔታ ያገኘ ፓርቲ ነው ያሉት ምሁራኑ፣ አዲሱን መንግሥት የሚመሠርተው ፓርቲ ሕዝብ የሰጠውን አደራ ለመወጣት ዝግጁ መሆን እንዳለበትም ለኢቢሲ በሰጡት አስተያየት አንስተዋል።

በምርጫ ሂደት አሸናፊም ሆነ ተሸናፊ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሕዝብ ድምፅ ወኪሎች በመሆናቸው፣ በቀጣይ የሀገር እና የሕዝብ ፍላጎት በሆኑ ብሔራዊ አጀንዳዎች ላይ በጋራ መሥራት እንደሚገባቸውም ምሁራኑ አሳስበዋል።

በተጨማሪም የምርጫው ሂደት ሙሉ በሙሉ እስኪጠናቀቅ እና የመጨረሻው ውጤት ይፋ እስኪደረግ ድረስ ኅብረተሰቡ የጀመረውን ሰላማዊ አካሄድ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

በአስረሳው ወገሼ