Search

ሰሞኑን በአርሲ እና ጎንደር የተፈጸሙ የሽብር ጥቃቶችን መንግሥት በጽኑ ያወግዛል፡- የሰላም ሚኒስቴር

ቅዳሜ ግንቦት 29, 2018 74

በአርሲ ዞን እና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በንጹኃን ዜጎችና በእምነት ተቋማት ላይ የተፈጸሙትን አሳዛኝ የሽብር ጥቃቶች መንግሥት በጽኑ እንደሚያወግዝ የሰላም ሚኒስቴር አስታወቀ። 

የሰላም ሚኒስትሩ አቶ መሀመድ እድሪስ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጡት መግለጫ ሀገራዊ ለውጡንና የሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ተከትሎ ተስፋ የቆረጡ ጽንፈኛ ኃይሎችና የውጭ ጠላቶች፥ የኢትዮጵያን ሰላምና የሕዝብ አብሮነት ለማፍረስ አደገኛ የትንኮሳ ካርዶችን እየመዘዙ መሆኑን አስታውቀዋል።

በአርሲ ዞን የሽብርተኛው የሸኔ ቡድን መጀመሪያ ከጸጥታ አካላት ጋር ግጭት መፍጠሩን ሚኒስትሩ ገልጸው፣ በአካባቢው ሕዝብ ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ በጀግንነት የተዋጉ 5 የሚሊሻ እና 3 የፖሊስ አባላት መስዋዕት መሆናቸውን ተናግረዋል።

በቡድኑ እኩይ ጥቃት ንጹሃን ዜጎች መገደላቸው እና አንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የተቃጠለች መሆኑን ጠቅሰዋል።

የጤና ጣቢያና የቀበሌ ጽህፈት ቤት መዘረፋቸው የተገለጸ ሲሆን በተጨማሪም 65 የመኖሪያ ቤቶች ወድመዋል።

መንግሥት እነዚህን ከኢትዮጵያውያን እሴት ያፈነገጡ ጥቃቶች በጽኑ እንደሚያወግዝ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ድርጊቱን መነሻ በማድረግ እውነታን ለማዛባትና ሀገራዊ ግጭት ለመቀስቀስ የሚደረገው የሚዲያና የሥነ-ልቦና ጦርነትም ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል።

በኦሮሚያ ክልል 6 ሺህ በላይ ታሪካዊ አድባራትና ገዳማት ያሉ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ ሕዝቡና የክልሉ መንግሥት ደህንነታቸውን ለመጠበቅ ሌት ተቀን እየሰሩ ባሉበት ሁኔታ፥ ጥቃቱን የሃይማኖት አስመስሎ ማቅረብ ተጠያቂነትን የሚያስከትል አደገኛ አካሄድ መሆኑን አሳስበዋል።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ የተፈጸመው ፈንጅ የማጥመድ ጥቃትም ሆነ የአርሲው እኩይ ተግባር፥ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ድምጽ የሰጠበትንና አፍራሽ ጥሪዎችን ሦስት ጊዜ ያከሸፈበትን ታሪካዊ የምርጫ ድል ለመቀማት የተወጠኑ ናቸው ብለዋል።

የእምነት ተቋማት የፖለቲካ ማስፈጸሚያ መሆን እንደሌለባቸው ያሳሰበው የሰላም ሚኒስቴር፤ ሕዝቡ የጥፋት ኃይሎችን የሚዲያ ማወናበድ በመመከት የአብሮነት እሴቶቹን እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርቧል።