7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አካል ጉዳተኞች ከመቼውም ጊዜ በላቀ ደረጃ በንቁ መራጭነትና በእጩነት የተሳተፉበት ታሪካዊ መድረክ መሆኑን የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን አስታወቀ።
ፌዴሬሽኑ የምርጫውን አጠቃላይ ሂደትና የተደራሽነት ሁኔታዎችን ከአባል ማህበራት ጋር በመተባበር በቅርበት ሲታዘብ መቆየቱን በሰጠው መግለጫ ገልጿል፡፡
በዘንድሮው የምርጫ ምዕራፍ 275 አካል ጉዳተኞች በዕጩነት ቀርበው መወዳደራቸውን ይፋያደረገው ፌዴሬሽኑ፣ ይህ ቁጥር በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ወቅት ከነበረው የ99 እጩዎች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር እጅግ ከፍተኛ መሻሻል የታየበትና የአካታችነት መርህን በተግባር ያሳየ መሆኑን ጠቅሷል።

በመራጮች ምዝገባ ረገድም ወደ 165 ሺህ የሚገመቱ አካል ጉዳተኞች ካርድ በመውሰድ የዜግነት መብታቸውን ለመጠቀም መመዝገባቸውን ተገልጿል፡፡
አጠቃላይ የምርጫ ሂደቱ ፍጹም ሰላማዊ ከመሆኑም ባለፈ የተደነገጉ ደንቦችንና መመሪያዎችን የተከተለ እንደነበርም ፌዴሬሽኑ አረጋግጧል።
በምርጫ ጣቢያዎች የተመደቡ አስፈጻሚዎች ለአካል ጉዳተኞች ከወትሮው በተሻለ መልኩ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠርና ድምፅ የመስጠት ቅድሚያ መብትን በማክበር ረገድ ያሳዩት ትጋት ለሂደቱ ስኬት ትልቅ አስተዋፅዖ ማበርከቱም ተነስቷል።
ፌዴሬሽኑ ለታየው በጎ ጅምር ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድና ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ምስጋናውን ያቀረበ ሲሆን፣ በቀጣይም አካል ጉዳተኞች ፖለቲካዊ መብቶቻቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲጠቀሙ የሚያስችሉ ሀገራዊ ጥረቶችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።