Search

የወጣቶች ንቁ የምርጫ ተሳትፎ እና የጎላ ድምፅ፤ ለነገዋ ኢትዮጵያ ግንባታና ለዲሞክራሲው ምዕራፍ አዲስ ተስፋ

ቅዳሜ ግንቦት 29, 2018 59

በኢትዮጵያ የተካሄደው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የወጣቶችን ሚና ወደ ላቀ ደረጃ ያሻገረና ኢትዮጵያን በጽኑ የዲሞክራሲ መሰረት ላይ ለመገንባት የሚያስችል ትልቅ አቅም የፈጠረ መሆኑን የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን አስታወቀ።

ኢትዮጵያውያን በነቂስ ወጥተው ድምጻቸውን የሰጡበት ይህ ታሪካዊ ምርጫ የሕዝብን ውሳኔ ማረጋገጡ ብቻ ሳይሆን፥ መላው የሀገራችን ወጣቶች በሂደቱ ላይ ያሳዩት ንቁ ተሳትፎ ለነገዋ የበለጸገች ሀገር ግንባታ አዲስ ተስፋ የሰነቀ መሆኑ ተገልጿል።

የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ተወካይ አቶ አሌክስአንደር ንጉሴ ከኢኮኖሚና ማህበራዊ እድገት ባለፈ የምርጫው በሰላም መጠናቀቅ የተረጋጋ ፖለቲካና የዳበረ የዲሞክራሲ ሥርዓት በሀገራችን መሬት እንዲይዝ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

ፌዴሬሽኑ በምርጫው ሂደት በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጣቶችን በታዛቢነት ከመመደብ ጀምሮ የመራጮች ትምህርት በመስጠት ረገድ ሰፊ ሥራዎችን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን በዚህም በድምሩ 32 ሺህ 500 ወጣቶችን በታዛቢነት እንዲሁም 2 ሺህ 500 ወጣቶችን በአስተባባሪነት በማሰማራት ታሪካዊ ኃላፊነቱን በብቃት መወጣቱን ገልጸዋል።

በየምርጫ ጣቢያዎቹ የተሰማሩት የፌዴሬሽኑ ታዛቢዎች ከተለያዩ የፖለቲካ ፖርቲዎች ተወካዮች፣ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና ከምርጫ አስፈፃሚዎች ጋር በቅንጅትና በገለልተኝነት መስራታቸው ለሂደቱ ስኬታማነት ከፍተኛ እገዛ ማድረጉንም አመላክተዋል።

ይህ አይነቱ የተደራጀ የወጣቶች ተሳትፎም ለመጪው ትውልድ የምትሆን አስተማማኝ ሀገርን ለማስረከብ በሚደረገው ጉዞ ውስጥ እንደ ትልቅ የሽግግር ምዕራፍ የሚቆጠር መሆኑ ተጠቅሷል።

በተለይም በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የተለያዩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወጣቶች በፖለቲካው መድረክ ላይ በስፋት እንዲሳተፉና እጩ ሆነው እንዲቀርቡ ዕድል የሰጡበት ሁኔታ መታየቱ ዘርፉን ይበልጥ ተስፋ ሰጪ እንደሚያደርገው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ይህ በፓርቲዎች የተወሰደው አወንታዊ እርምጃ ወጣቶች የሀገራቸውን ዕጣ ፈንታ በራሳቸው የፖለቲካ ተሳትፎና የብስለት ድምፅ እንዲወስኑ በር የከፈተ በመሆኑ፥ ምርጫው የኢትዮጵያውያን መምረጫ ብቻ ሳይሆን የሀገራዊ አንድነትና የዲሞክራሲ አሸናፊነት ማሳያ ሆኖ እንዲመዘገብ አስችሎታል ብለዋል።