በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገውን የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ የኢትዮጵያ የታክስ ገቢ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) ያለው ድርሻ በ2018 በጀት ዓመት ወደ 9.5 በመቶ ከፍ ይላል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴ አስታወቁ።
ሚኒስትሩ ይህንን የገለጹት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 25ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የ2019 በጀት ዓመት መነሻ ዕቅድን ለውይይት ባቀረቡበት ወቅት ነው።
አቶ አሕመድ ሽዴ ለምክር ቤቱ እንደገለጹት፣ የግብር አሰባሰብን ለማሳለጥ እና የታክስ ፍትሐዊነትን ለማረጋገጥ የወጣው ብሔራዊ የመካከለኛ ዘመን ስትራቴጂ ውጤት እያስገኘ ነው።
በዚህም መሠረት ከበርካታ ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በ2017 በጀት ዓመት ሀገራዊ የታክስ ገቢ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ጋር ያለው ጥምርታ በ1.6 በመቶ በመጨመር፣ በ2016 ከነበረበት 6.2 በመቶ ወደ 7.7 በመቶ ከፍ ማለቱን አብራርተዋል።
ይህ አፈጻጸም በ2018 በጀት ዓመትም ተጠናክሮ በመቀጠሉ ድርሻው ወደ 9.5 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚገመት አመልክተዋል።
ለዚህ ስኬት የተጨማሪ እሴት ታክስ፣ የኤክሳይዝ ታክስ እና የገቢ ግብር አዋጅ ማሻሻያዎች እንዲሁም የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ሥርዓት ማሻሻያ መደረጉ በዋናነት ይጠቀሳሉ።
ሚኒስትሩ አክለውም ከዚህ ቀደም በጥቅሉ ሲሰጡ የነበሩ እና ተገቢውን ውጤት የማያመጡ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችን በመቀነስ፣ ማበረታቻው ኢንቨስተሮች በሀገር ውስጥ ከሚያስመዘግቡት የሥራ ዕድል፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የካፒታል ፈጠራ ጋር በቀጥታ እንዲገናኝ መደረጉ ሀገራችን ታጣው የነበረውን ከፍተኛ ገቢ ለማስቀረት ማስቻሉን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የመንግሥት የፊስካል ጉድለት መጠን ከፍተኛ መሻሻል ማሳየቱን የጠቀሱት አቶ አሕመድ በ2017 በጀት ዓመት በ7 ዓመታት ውስጥ ዝቅተኛው የበጀት ጉድለት መመዝገቡን ይፋ አድርገዋል።
ይህም ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (GDP) አኳያ አንድ በመቶ ብቻ መሆኑን እና በ2014 ዓ.ም ከነበረበት 4.1 በመቶ አንጻር ሲታይ እጅግ ከፍተኛ መሻሻል መሆኑን አስረድተዋል።
በበረከት ሽመልስ