እያደሩ መጣፈጥ ለእርሱ የተፈጠረ ይመስላል። የትናንቱ ጨዋታ ውጤት የመጨረሻው መጀመሪያ ምልክት እንጂ፤ የድል መጀመሪያ አይደለም፤ ፍጻሜም አይመስልም።
የሮዛሪዮ ሳንታፌው ልጅ ሊዮኔል አንድሬስ ሜሲ፣ ከ23 ዓመታት በፊት ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አንስቶ አርጀንቲናን ወክሏል።
ይህ ከመሆኑ በፊት በስፔን ካታሎኒያ የሚገኙት የሜሲ ዘመዶች፣ ገና በአፍላ ዕድሜው በትውልድ ቀዬው ሮዛሪዮ ያሳየውን የእግር ኳስ ተሰጥኦ ተመልክተው ዕድል በማመቻቸታቸው፤ ወደ ግዙፉ የባርሴሎና ክለብ የሚያደርሰውን የላማሲያ ታዳጊዎች ማሰልጠኛን ሊቀላቀል ችሏል።
ከዚህ በኋላ 'ድንቁ ባለ ግራ እግር ተጫዋች በእግር ኳሱ ዓለም ምን አደረገ?' የሚል ጥያቄ ከተነሳ፤ መልሱ “የቀረው ታሪክን ነው” የሚል ይሆናል።
አሁን ደግሞ ወደ ‘አልቢሴሌስቴዎቹ’ መንደር፣ ወደነ ዲዬጎ አርማንዶ ማራዶና ቅጽር እንዝለቅ።


ሜሲ በግራ እግሩ የዓለምን እግር ኳስ ወደ ሌላ ምዕራፍ ሲያሻግር የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን ግን ለዚህ ስኬት ሳይታደል ቆይቷል።
በካታሎኒያ እንደተደጋገሙት ሜሲን የተንተራሱ ድሎች፤ ቦነስ አይረስ ሳትቋደሳቸው ረጅም ዓመታት ነጎዱ።
ቡድኑን ለዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ያበቃ ውጤት ቢያስመዘግብም፣ ከዋንጫው ጋር ግን ተራራቀ። በዚህም አርጀንቲናውያን ክፉኛ አዘኑ።
ሜሲ እነዚህ ጫናዎች ሲከብዱት እና በውኃ ሰማያዊው መለያ ልክ እንደ ካምፕ ኑው ውጤት አልሰምር ሲለው፤ 'ቢበቃኝስ' እስከማለት ደረሰ።
ውሳኔውን ተከትሎም የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድንን መለያ ዳግም እንደማይለብስ አስታወቀ። ይህ በወቅቱ እጅግ አስደንጋጭ ዜና ነበር።
ከ2016ቱ የኮፓ አሜሪካ ሽንፈት በኋላ የመጣው ይህ የሜሲ ውሳኔ እንዲቀለበስ፤ የወቅቱ የአርጀንቲና ፕሬዝዳንት ማውሪሲዮ ማክሪ እና ኮከቡ ዲዬጎ ማራዶና ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ሜሲ ወደ ብሔራዊ ቡድኑ ተመለሰ።
የተመለሰበት ዋና ዓላማ ደግሞ፣ ከእጆቹ ያመለጠውን የኮፓ አሜሪካ እና ትልቁን የዓለም ዋንጫ ለአልቢሴሌስቴዎቹ ማምጣት ነበር።
ይህንኑ ጥያቄ በ2021 ኮፓ አሜሪካን፣ በ2022 ደግሞ የዓለም ዋንጫን በማንሳት በተግባር መለሰ።
ያኔ ሜሲ ከዚህ በኋላ እግር ኳስን ቢሰናበት እንኳን፣ የስኬት መንገዱ ወደ ምሉዕነት ተጠግቷል የሚለው ሀሳብ ብዙዎችን አስማምቶ ነበር።
እርሱ ግን 'በቃኝ' ማለትን አልወደደም። በግልም ሆነ በቡድን፣ በክለብም ሆነ በብሔራዊ ቡድን፤ በድል ላይ ድል፣ በክብረ ወሰን ላይ ሌላ ክብረ ወሰን እየደራረበ መጓዙን ቀጥሏል።
በ2024 የኮፓ አሜሪካ ውድድር ላይም ተከታታይ ስኬቱን አስመዝግቦ፣ በአሜሪካ ምድር ወደሚካሄደው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጉዞውን ቀጥሏል።
ሌሊቱን አርጀንቲና ካንሳስ ላይ አልጄሪያን ገጥማ 3 ለ 0 ስታሸንፍ፤ አሁንም ቡድኑ በሜሲ ትከሻ ላይ እንዳለ ባሳበቀ ሁኔታ ሦስቱንም ግቦች ያስቆጠረው እርሱ ነው።
ይህም በብሔራዊ ቡድን መለያ 11ኛ ሀትሪኩ ሆኖ ተመዝግቧል። በዓለም ዋንጫ ታሪክም ሀትሪክ የሰራ አንጋፋው ተጫዋች ለመሆን በቅቷል።
የዓለም ዋንጫ አዳዲስ ኮከቦችን እንደሚያስመለክተው ሁሉ፤ እንደ ሜሲ ያሉትን የዘመን ክስተቶችም ማንገሱን ቀጥሏል። በእርግጥ 23 ዓመታት በእግር ኳስ ውስጥ እጅግ ብዙ ናቸው።
በእነዚህ ሁሉ ዓመታት የስኬት ምሳሌ እየተደረጉ መቀጠል ደግሞ እንደ ሜሲ ላሉ ጥቂት ተሰጥኦዎች እንጂ ለብዙዎች የሚቻል አይደለም።
'የ21ኛው ክፍለ ዘመን እግር ኳስ እርሱ ባይኖረው ምን ሊመስል ይችላል?' የሚል ጥያቄ ሲነሳ፤ “ታሪኩ አሁን ካለው የተለየ መልክ ይኖረው ነበር” የሚል መልስ መከተሉ አይቀርም።
“በሕይወት እስካለሁ፣ ጉልበቴ እስካልዛለ፣ ጤናዬም እስካልተጓደለ ድረስ ለምወዳት እግር ኳስ ያለኝን ሁሉ እሰጣለሁ” ይህ ቃል፤ ከጨዋታው በኋላ የሰነዘረው ቁልፍ ሀሳብ ነው።
ሊዮኔል ሜሲ የመጀመሪያ የዓለም ዋንጫ ግቡን ባስቆጠረበት የ2006 ውድድር እና በትናንቱ ሀትሪኩ መሀል የ20 ዓመታት ልዩነት አለ።
አሁን ላይ በዓለም ዋንጫ መድረክ ለአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን በዕድሜ ትንሹም ሆነ አንጋፋው ግብ አስቆጣሪ መሆን የቻለው እርሱ ነው።
በእድሪስ አህመድ