ኢቢሲ በራሱ አቅም ያበለጸገውን የሞባይል መተግበሪያ በትናትናው እለት በይፋ አስመርቆ ወደ አገልግሎት አስገብቷል።
በዚህ ሁነት ላይ የተገኘው አትሌት ገዛኸኝ አበራ በሰጠው አስተያየት፤ ኢቢሲ ሁልጊዜም ሮጠን ስናሸንፍ አብሮን ነበር ሲል ይገልጻል፡፡
ኢቢሲ እንደአሁኑ ሚዲያዎች ባልበዙበት ጊዜ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሀገር አቀፍም ሆነ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ በሚሳተፉበት ወቅት የዜና ሽፋን በመስጠት ለአድማጭ ተመልካቾች በማድረስ ትልቅ ሚና እንደነበረው አትሌቱ ይናገራል፡፡
ዲጂታል ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ኢቢሲ በራሱ አቅም ያበለጸገው መተግበሪያ ከዚያ በፊት የነበሩ አሰራሮችን ይበልጥ በማቅለል ወደ ተመልካቾቹ ይበልጥ ለመቅረብ እንደሚያስችለውም አትሌት ገዘኻኝ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
ኢቢሲ አንጋፋ የሚዲያ ተቋም መሆኑን የገለጸው አትሌት ገዘኻኝ፤ ሮጠን ስናሸንፍ መጀመሪያ ቃለ መጠይቅ የምንሰጠው ለኢቢሲ ነበር ሲልም ትውስታውን ያጋራል፡፡
የኢቢሲ ዲጂታል መተግበሪያ ይፋዊ የምርቃት ፕሮግራም ላይ በመታደሙ ደስተኛ መሆኑን የገለፀው አትሌቱ፤ በዚህ የዲጂታል ዓለም ውስጥ በመኖሬ እድለኛ ነኝ ሲልም ተናግሯል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጅራ በበኩላቸው፤ ኢቢሲ በዲጂታል መተግበሪያ መምጣቱ ከአናሎግ ወደ ዲጂታል የተደረገ የአስራር ለውጥ ማድረጉን ያመላክታል ብለዋል፡፡
ለውጡ በፍጥነት መረጃ ተደረሽ ለማድረግ ከማገዙም ባሻገር በቀላሉ መረጃ ለማግኘት የሚያግዝ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ኢቢሲ ቀዳሚው የስፖርት መረጃ ምንጭ ነው ያሉት አቶ ኢሳያስ፤ መተግበሪያው ማህበረሰቡ በስራ ቦታው እንዲሁም በማንኛውም ስፍራ ላይ ሆኖ በቀላሉ በስልኩ የሚፈልገውን መረጃ ማግኘት እንዲችል ያግዛል ብለዋል፡፡
በመሀመድ ፊጣሞ እና ንፍታሌም እንግዳወርቅ
#EBC #ebcdotstream #Digital_EBC #DigitalEthiopia #EBCApp