Search

ከፍፃሜ በፊት ያለ ሌላ ፍፃሜ፤ ሀዘንን መርሻ፣ አጨራረስን ማደሻ!

ቅዳሜ ሐምሌ 11, 2018 128

በ23ኛው ዓለም ዋንጫ ፍፃሜ ዋዜማ ላይ ቆመናል። ዓለም ዋንጫ በግማሽ ፍፃሜ በለስ ያልቀናቸውን፣ ድል ከነርሱ ጋር ያልነበረውን እንዲሁ አያሰናብትም። ለሦስተኝነት ማዕረግ ዳግም ያፋልማል።

23ኛው ዓለም ዋንጫ ፍሎሪዳ ላይ የግማሽ ፍፃሜ ተሸናፊዎቹን ዛሬ እኩለ ሌሊት 6፡00 ሰዓት ፍሎሪዳ ሚያሚ ላይ ያፎካክራል። በእርግጥ በብዙዎች፣ በተለይም በተሸናፊ ብሔራዊ ቡድኖች ዘንድ የደረጃው ጨዋታ ለመጫወት የተመረጠ አይደለም።

የዛሬው መርኃ ግብር ግን ብሔራዊ ቡድኖቹ ከሚያደርጉት ፉክክር ባልተናነሰ፣ በኮከብ ግብ አስቆጣሪነት በመላቅ የወርቅ ኳስ ሽልማቱን ለማግኘት ባለው ፉክክር ለውጥ እንደሚያስከትል ይጠበቃል። ከሊዮኔል ሜሲ ጋር የኮከብ ግብ አስቆጣሪነት ፉክክሩን በ8 ግቦች እየመራ የሚገኘው ኪሊያን ምባፔ እንዲሁም እያንዳንዳቸው ስድስት ግቦች ያስቆጠሩት ጁድ ቤሊንግሃም እና ሀሪኬን ከባለ አምስት ግቡ የዓለም ኮከብ ኡስማን ዴምቤሌ ጋር በሚያደርጉት የኮከብ ግብ አስቆጣሪነት ፉክክር ላይ አንዳች ለውጥ ሊያስከትል የሚችል ጨዋታ እንደሚሆን ታምኗል።

በዚህ መሀል ግን ከሽንፈት ማግስት የሚደረግ፤ ከዓለም ዋንጫ ስንብት ሀዘንም ሳያገግሙ የሚመጣ መርኃ ግብር መሆኑ የተጫዋቾችን ተነሳሽነት መቀነሱ፣ የተመልካቾችን ጉጉትም ማሳነሱ አይቀርም። ቶማስ ቱሄል ይህን የሚያስረግጥ ሃሳብ ነው የሰነዘሩት። "የእኛም ሆነ የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ይህን ጨዋታ የማድረግ ፍላጎት የላቸውም" በማለት በውድድሩ ሙሉ የለፉትና የተዘጋጁት ለዓለም ሻምፒዮንነት በመሆኑና፤ ያም ባለመሳካቱ ለዚህ ጨዋታ የሚኖራቸውን ጉጉትና ፍላጎት እንደቀነሰው ተናግረዋል።

ቱሄል ይህንን ቢሉም የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዲዲየር ዴሻው ግን ከዚህ በአንፃራዊነት የተለየ ሃሳብ ነው የሰነዘሩት። 3ኛ ደረጃም ቢሆን የተሻለ መሆኑን በማንሳት፤ እርሱን ለማሳካት የቻሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። አክለውም የተፈጠረው ሀዘን የዓለም ሻምፒዮን ከመሆን ፅኑ መሻት የመጣ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሆነውን ከመቀበል ውጪ አማራጭ የለንም ብለዋል።

በግማሽ ፍፃሜው እንግሊዝ እየመራች የነበረችውን ጨዋታ የኋላ ኋላ በአርጀንቲና 2 ለ 1 ተሸንፋ የፍፃሜ መንገዷ ሲቋረጥ፤ በአንፃሩ ፈረንሳይ ባልተጠበቀ ሁኔታ በስፔን ፍፁም ብልጫ ተወስዶባት 2 ለ 0 ተረታ ነው ከፍፃሜው የቀረችው። 

የ23ኛው ዓለም ዋንጫ 103ኛው ጨዋታ በሁለት ሃሳቦች መሀል፤ የጨዋታውን አስፈላጊነት ተጠይቅ ውስጥ በሚከቱና የኮከብ ግብ አግቢነት ፉክክሩ ላይ የሚኖረውን ሚና በሚያጎሉ መሀል ሆኖ፤ እኩለ ሌሊት 6፡00 ሰዓት በሚያሚ ጋርደን ሀርድ ሮክ ስታዲየም ይካሄዳል።

በዚህ የደረጃ ጨዋታ ማን የሚያሸንፍ ይመስላችኋል? ግምታችሁን አጋሩን 

በእድሪስ አህመድ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: