የመደመር መንግሥት በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከፍተኛ የሕዝብ ድምፅ በማግኘት ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ሀገርን ለመምራት በይፋ ተመሥርቷል።
የምርጫው ውጤት የሕዝቡን የለውጥ ተስፋና የልማት ፍላጎት የሚያንጸባርቅ ሲሆን፣ በመንግሥትና በአዲሶቹ የሕዝብ ተወካዮች ላይ ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት ጥሏል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለኢቲቪ እንደገለጹት፣ የቀጣዮቹ 5 ዓመታት ዋነኛ ተልዕኮ ሀገራዊ ሰላምን በማረጋገጥ የልማት ሥራዎችን ማፋጠን ነው።
በቀጣይ በሀገራችን የተሟላ ሰላም እንዲሰፍንና ኅብረተሰቡ ሙሉ ትኩረቱን በልማት ላይ እንዲያውል አቅጣጫ መስጠትና መሥራት የመንግሥት ዋነኛ ኃላፊነት መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ማህተመ ኃይሌ (ዶ/ር)፣ ኅብረተሰቡ ለመረጠው ፓርቲ ያለው እምነት ከፍተኛ ኃላፊነትን የሚያስከትል መሆኑን ጠቁመው፣ ፓርቲውም ሕዝቡ በምርጫ የሰጠውን አደራ በታማኝነት መወጣት እንደሚጠበቅበት መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ቲጃኒ ናስር፣ የኑሮ ውድነትንና ሥራ አጥነትን መቀነስ ሕዝቡ ከመንግሥት ከሚጠብቃቸው ዋነኛ ተግባራት መካከል እንደሆኑ ገልጸዋል።
የውሃ ሀብትን ጨምሮ ሀገራችን ያላትን የተፈጥሮ ሀብት፣ መሬትና የሰው ኃይል በአግባቡ በማልማት ወደ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም መቀየር እንደሚገባም አመላክተዋል።
ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎን በማጠናከርና የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ረገድ የተወሰዱ እርምጃዎችም በቀጣይ ይበልጥ መጠናከር እንዳለባቸው የምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ሙስሊማ ረሺድ፣ በ7ኛው ምርጫ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ተሳትፎ መጨመሩ የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋቱን አመላካች ነው ብለዋል።
የፖለቲካ ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት ሀገርን በጋራ ለማሻገር በትብብር መሥራት እንደሚገባም ተናግረዋል።
ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይዛ ያለባሕር በር መቀጠሏ አሳሳቢ መሆኑን ጠቅሰው፣ መሻታችንን በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማሳካት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመላክተዋል።
ውስጣዊ ችግሮችንና የፖለቲካ ልዩነቶችን ከኃይል ይልቅ በሰላማዊ ድርድር መፍታት እንደሚገባም ገልጸዋል።
ለአዲሱ የመደመር መንግሥት በምርጫ የተሰጠው አደራ ሰላምን በማጽናትና ሀገራዊ ጥቅምን በማስከበር ረገድ የተጣለበት ኃላፊነት መሆኑንም አስገንዝበዋል።
የቀጣዮቹ 5 ዓመታት ስኬትም በተሰጠው አደራ መሠረት በተግባር በሚመዘገቡ ውጤቶች፣ በሰላም ግንባታና በሕዝብ ተጠቃሚነት የሚለካ የሆናል።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: