ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመንግሥት ምሥረታ ወቅት ያደረጉት ንግግር በተለያዩ የዓለም ቀጣናዎች የኢትዮጵያን ተፅዕኖ ፈጣሪነት ከማሳየት ባለፈ፣ የመደመር መንግሥት ቀጥሎ ለሚያከናውነው ሥራ ፍኖተ ካርታ ሊሆን የሚችል ጠንካራ መልዕክት መሆኑን የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ።
በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዘኛ ቋንቋ እና ሥነ ጽሑፍ መምህር እና ተመራማሪ ተመስገን ቶራ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ንግግር ትናንትን ያሳየ፣ ዛሬን እንድናውቅ የረዳ እና ነገን መቀጠል የምንችልባቸውን መንገዶች የጠቆመ ጥልቅ ይዘት ያለው ነው። በመሆኑም መጪውን ጊዜ ጭምር በመጠቆም እንደ ፍኖተ ካርታ ሊያገለግል የሚችል ጥልቅ መልዕክት በውስጡ ይዟል ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው የኢንጂነሪንግ ኮሌጅ የውኃ ሀብት እና መስኖ ምህንድስና መምህር ንጋቱ ቶማ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ንግግራቸው ቀጥሎ ባለው ጊዜ ኢትዮጵያ ከችግር ተላቅቃ ራሷን ወደ መቻል እንደምትገባ እና ችግሮች ሲያጋጥሙን ተቋቁመን ማለፍ እንደምንችል ያሳየ ነው ብለዋል። በዚህም ኢትዮጵያውያን የተሻለ ተስፋ እንድንሰንቅ ያደርጋል ሲሉ ተደምጠዋል።
ችግሮችን እንደ መልካም አጋጣሚ በማየት ሀገር በቀል መፍትሔ ለችግሮቻችን ማሳየት እንደምንችል ያሳየ መልዕክት ማስተላለፍ መቻላቸውን የገለጹት ደግሞ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የአካውንቲንግ እና ፋይናንስ መምህር እና ተመራማሪ ተመስገን ተስፋዬ ናቸው። የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም ውጤት ለዚህ ማሳያ መሆኑን አንሥተዋል።
በዩኒቨርሲቲው በአካውንቲንግ እና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት መሰለ ከበደ (ዶ/ር)፣ ንግግራቸው ኢትዮጵያ በጽናትና በትጋት ወደ ላቀ የሥልጣኔ ምዕራፍ እንደምትደርስ ያሳየ ተግባር ተኮር ተስፋ በውስጡ አካትቶ መያዙን ጠቁመዋል።
ምሁራኑ ኢትዮጵያ ወደምታልመው ከፍታ እንድትደርስ ለማስቻል በመደመር መንግሥት የተጀመሩ ሁለንተናዊ የለውጥ ተግባራትን ሁሉም ዜጎች መደገፍ አለባቸው ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በተመስገን ተስፋዬ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: