Search

"መረር ያሉ እርምጃዎች ይቀጥላሉ"፦ ከቃላት ያለፈ የተግባር እርምጃ

እሑድ ጥቅምት 01, 2019 61

ኢትዮጵያ የምትሻውን ብልፅግና ለማሳካት መልካም አስተዳደር እና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ  ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው።

የሌብነት፣ የሙስና፣ የዘመድ አሠራር እና የወገንተኝነት ድርጊቶች የሕዝብን እምነት የሚያሸረሽሩ፣ ሀብትን የሚያባክኑ እና የልማት ሥራዎችን የሚያሰናክሉ ዋና ዋና ተግዳሮቶች ናቸው።

በመደመር መንግሥት ምሥረታ ላይ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሙስናን፣ ሌብነትን፣ የዘመድ አሠራርን እና ወገንተኝነትን ለማስወገድ የተጀመሩ መረር ያሉና አስተማሪ እርምጃዎች አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በግልጽ አስታውቀዋል።

ይህ አቋም የመደመር መንግሥት ለተቋማዊ ጥራት፣ ለፍትሕ እና ለሀገራዊ ሀብት ጥበቃ ያለውን የማይናወጥ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።

የመደመር ፍልስፍና ሀገራዊ ዕድገትን እውን ለማድረግ የሰው ኃይልን፣ ዕውቀትን እና ሀብትን አስተባብሮ መጠቀምን አልሞ የሚንቀሳቀስ እሳቤ ነው።

በዚህ እሳቤ ውስጥ ሙስና እና ሌብነት የኢትዮጵያን አቅም የሚያደናቅፉ፣ የዜጎችን እኩል ተፎካካሪነት የሚያጠፉ የዕድገት ደንቃራዎች ተደርገው ይታያሉ።

ለሙስና እና ለሌብነት የተሰጠው ምላሽ በቃላት ከሚደረግ ወቀሳ ባለፈ በተግባር የተደገፉ በርካታ እርምጃዎችን በማስከተል ላይ ይገኛል።

ብሔራዊ የፀረ-ሙስና ኮሚቴ ከማቋቋሙ ባሻገር ፍትሕን የሚያዛቡ፣ የታማኝነት እና የሥራ እሴቶችን የሚሸረሽሩ አሠራሮች በየትኛውም የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ቦታ ሊኖራቸው እንደማይገባ በመርሕ ደረጃ ተቀምጧል።

በከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነት ላይ የነበሩ፣ በትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች እና በበጀት አስተዳደር ላይ ምዝበራና ዝርፊያ ፈጽመዋል የተባሉ ግለሰቦችን እና መረቦችን በሕግ አሠራር መሠረት ተጠያቂ በማድረግ የፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲያገኙ ተደርጓል።

ከዚሁ ጎን ለጎን የአገልግሎት አሰጣጥን ግልጽ፣ ዘመናዊ እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተደገፉ በማድረግ፣ የሰው ልጅ ጣልቃ ገብነትን በመቀነስ የሌብነት እና የሙስና ዕድሎች በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንሱ እየተሠራ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት ወደፊት የሚወሰዱት መረር ያሉ እርምጃዎች የመንግሥትን የልማት እና የፍትሕ አጀንዳ የሚያስፈጽሙ እንጂ ለማንም ወገን አድልኦ የሚያደርጉ አይሆኑም።

ይህም ኢትዮጵያ የጀመረችውን አዲስ የሥልጣኔ እና የብልጽግና ጉዞ ግልጽ በሆነና በታማኝ አስተዳደራዊ መዋቅር ላይ ለማቆም ታላቅ ዋስትና ይሆናል።

በሃና ምንዳሁን

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: