በኦሮሚያ ክልሉ ከ6 ሺህ ሄክታር በታች በሆነ መሬት ላይ የተጀመረው የሩዝ ልማት ኢኒሼቲቭ በ2018 ዓ.ም ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መድረሱን የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያመለክታል።
በክልሉ በጅማ፣ በኢሉአባቦር፣ በቡኖ በደሌ እንደዚሁም በወለጋ የሩዝ ምርት በስፋት እየተመረተ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ሀላፊ ጌቱ ገመቹ ገልጸዋል።
ቀደም ሲል ከውጭ ይገባ የነበረውን የሩዝ ምርት በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ታስቦ ወደ ተግባር መገባቱንም አቶ ጌቱ አስታውሰዋል።
በ2017 ዓ.ም የምርት ዘመን በክልሉ በሩዝ ከተሸፈነው መሬት ከ52 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢቲቪ ያነጋገራቸው የጅማ ዞን፣ ሸቤ ሶምቦ ወረዳ፣ ኪሼ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ጀማል እድሪስ እና አርሶ አደር አዲሱ ሙሳ፥ የሩዝ ሰብል ከዚህ ቀደም ከሚዘሩዋቸው የተለያዩ አዝርዕት በተሻለ መልኩ ውጤታማ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።
ከዘንድሮው የምርት ዘመን የተሻለ የሩዝ ምርት እናገኛለን ብለው እንደሚጠብቁም ተናግረዋል።
በዘንድሮው ዓመት ከሚያገኙት ምርት በመነሳትም በቀጣይ በሰፊ ማሳ ላይ ሩዝ የማምረት ሀሳብ እንዳላቸው ጠቁመዋል።
በወረዳው ቀድሞ ከሚታወቁ የሩዝ ዝርያዎች በተጨማሪ 14 አዳዲስ የሩዝ ዝርያዎች ቀርበው ስድስቱ በስራ ላይ መዋላቸውን የሸቤ ሶምቦ ወረዳ ግብርና ባለሙያዎች ለኢቲቪ ገልጸዋል።
በራሔል አብደላ
#ebcdotstream #etv #oromia #rice