የዓለም የስኳር ሕመም ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ35ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ እና በአፋር ክልል የስኳር ሕሙማን ማኅበራት አዘጋጅነት በሰመራ ተከብሯል።
ቀኑ “ስኳር ሕመም እና ደህንነት፣ በሥራ ቦታ ስለ ስኳር ሕመም ይበልጥ ይገንዘቡ፣ ተጨማሪም ድጋፍ ያድርጉ” በሚል መሪ ሐሳብ ተከብሯል።
የኢትዮጵያ ስኳር ሕሙማን ማኅበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ጌታሁን ታረቀኝ፥ በኢትዮጵያ የስኳር ሕሙማን ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ የስኳር ሕመም እንዳለባቸው የማያውቁ ሰዎች ሲጨመሩ ደግሞ ቁጥሩ ከዚህም ከፍ እንደሚል ተናግረዋል።
ዜጎች ስለ ሕመሙ ግንዛቤ እንዲያገኙ እና ተመርምረው ራሳቸውን እንዲያውቁ ማኅበሩ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከክልል ጤና ቢሮዎች እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ለውጥ ለማምጣት እየሠራ እንደሚገኝ ዶክተር ጌታሁን ገልጸዋል።
በአፋር ክልል የስኳር ሕሙማን ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን የጠቀሱት የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ተወካይ እና የበሽታ መከላከል ዳይሬክተር አሊ አህመድ በበኩላቸው፤ ኅብረተሰቡ ጤናውን በአግባቡ ከመጠበቅ አኳያ ያሉትን ክፍተቶች ለመቀነስ በክልሉ በሚገኙ ሆስፒታሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የምርመራ ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የዓለም የስኳር ሕመም ቀንን አስመልክቶ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ የእግር ጉዞ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይቶች እና የነፃ ምርመራ ዘመቻ ተካሂዷል።
በሁሴን መሐመድ