ቃታ ከመሳብ፣ ወንበር መሳብ እንደሚቀል፤ በየበረሀው ከመንከራተት፣ በአዳራሽ ሆኖ በመፍትሔዎች ላይ መወያየት እንደሚበጅ መንግሥት በተደጋጋሚ ተናግሯል፤ በተግባርም አሳይቷል።
በዓለም ላይም ውጤታማው የትግል ስልት በመባል የሚታወቀውም ይህ ነው ሲሉ በኢቲቪ የሀገር ጉዳይ ፕሮግራም ላይ የተሳተፉ ምሁራን እና የፖለቲካ ተንታኞች ተናግረዋል።
“ከጦረኞቹ ጀርባ ምን እየተካሄደ ነው?” በሚል ርዕስ ከኢቲቪ የሀገር ጉዳይ ፕሮግራም ጋር ቆይታ ያደረጉት የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም፥ ነፍጥ አንስተው ወደ ጫካ የገቡ ታጣቂዎች፣ የትጥቅ ትግልን ዋንኛ የገቢ ማግኚያ መንገድ አድርገውታል ብለዋል።
በዋናነት እየጎዱ ያሉት እንታገልለታለን የሚሉትን ማኅበረሰብ ነው ያሉት ፕሮፌሰር አለማየሁ፤ የነፍጥ ፖለቲካ ዋንኛ መተዳደሪያ የሆናቸው ታጣቂዎች፣ ወደ ሰላማዊ ትግል ለመመለስ ፍላጎታቸው እምብዛም ነው ሲሉ ገልጸዋል።
“እነዚህ ኃይሎች ቀድሞውኑ ወደ ትጥቅ ትግል የገቡት አማራጭ ጠፍቶ ነው ወይ?” ብሎ መጠየቅ እንደሚገባ የጠቆሙት ፕሮፌሰሩ፤ እውነታው ግን እነዚህ አካላት ኢትዮጵያ የውስጥ ሰላሟ እንዲደፈርስ በውጭ ጠላቶቻችን የተገዙ እና የሰላም አማራጮችን ችላ ብለው ወደ ጫካ የገቡ መሆናቸው ነው ሲሉ ተናግረዋል።
እነርሱ ትግል በሚሉት አደረጃጀት ውስጥ ያለው ታጣቂ ኃይል፣ እየታገልኩለት ነው የሚለውን ማኅበረሰብ እያገተ እና እየዘረፈ እንዲሁም ከውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ምፅዋት እየተቀበለ መኖርን ምርጫው ያደረገ ነው ብለዋል።

የፖለቲካ ጥያቄ ነፍጥ ካስነሳ፣ ፖለቲካነቱ ያበቃል ያሉት ደግሞ የፖለቲካ ተንታኙ አፈወርቅ በደዊ ናቸው።
እርሳቸው እንደሚሉት፥ መንግሥት የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት እና በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ በማድረግ ጦርነትን ለማስቀረት የሚታይ ተጨባጭ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። በታጣቂዎች በኩል ግን የሰላም ፍላጎት እምብዛም አይታይም።
ወጣቱ መረጃን በማጣራት እና ምንጩን በመለየት ከውጭ ሆነው ሐሰተኛ መረጃ እና የጥላቻ ንግግር በሚያሰራጩ አካላት የሴራ መረብ እንዳይጠለፍ ራሱን መጠበቅ እንዳለበት ምሁራኑ ምክረ ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል።
በሀብተሚካኤል ክፍሉ
#ebcdotstream #armedconflict #የሀገርጉዳይ #yehagerguday