የወሎ መንዙማን ድንበር ተሻጋሪ በማድረግ ረገድ እንደ መሐመድ አወል ሀምዛ ያለ ባለታላቅ አሻራ ማግኘት አዳጋች ነው። መሐመድ አወል የጥበብ ሰው ብቻ ሳይሆን፣ መንዙማን በአማርኛ ቋንቋ ለኢትዮጵያውያን ጆሮ ያደረሰ የዘመኑ የዜማ መሃንዲስ ነው።
በተለይ በ1987 ዓ.ም የመጀመሪያውን የአማርኛ መንዙማ በካሴት አሳትሞ ሲያወጣ፣ የሀገራችንን መንፈሳዊ የኪነ-ጥበብ ጉዞ አዲስ ምዕራፍ አስጀምሯል።
የመሐመድ አወል ድምፅ የሚያስገመግም፣ ቀልብን ሰብስቦ ሌላ ዓለም ውስጥ የሚከትና ነፍስን የሚያረሰርስ ልዩ ኃይል አለው።
በተለይ በእንጉርጉሮዎቹ ውስጥ የሚታየው የዜማ ፍሰትና የቃላት ውህደት እጅግ አስደናቂ ነው። ጥልቅ የሆኑ የሐዲስና የታሪክ ድርሳናትን፣ ፊደል ላልቆጠሩ ወገኖች ሳይቀር በቀላሉ እንዲረዱት አድርጎ በዜማና በግጥም አዋድዶ የማቅረብ ምትሃታዊ ችሎታ አለው።
ከጀሊሉ ልዕልና እስከ ነብያት ሙዕጂዛ፣ ከሕይወት ፍልስፍና እስከ ሞትና ከእምነት እስከ ማኅበራዊ ትስስር ያልዳሰሰው የሕይወት ዘርፍ የለም።
ይህ ድምጸ-በረከት ሙስሊሙን ብቻ ሳይሆን፣ የክርስቲያኑንም ጆሮና አንጀት የሚጎትት የወሎ የጥበብ ልህቀት መገለጫ ነው።
መሐመድ አወል የጥንቱን ዘመን ከዛሬው ጋር ያቆራኘ፣ የአበሻን ሙፍቲ ትርክትና ትንግርት በድምፁ ለሕዝብ ያጋባ ታላቅ ዓሊም ነው።
የእሱ ሥራዎች ዘመን የማይሽራቸው ተሻጋሪ ቅርሶች በመሆናቸው፣ በተለይ የእንጉርጉሮ ሥራዎቹን ያልሰማ ሰው ትልቅ የጥበብ ገበታ አምልጦታል። መሐመድ አወል ሀምዛ የወሎ መንዙማ ዳግም ሰሪና የጥበብ ወሰን ሆኖ ለዘላለም ይኖራል።