Search

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና አገልግሎቱን ለማዘመን ከኮሪያ ኤክስፖርት-ኢምፖርት ባንክ ጋር የተደረገውን የብድር ስምምነት አጸደቀ

ማክሰኞ መጋቢት 15, 2018 57

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 12ኛ መደበኛ ስብሰባ፣ የጤና ዘርፉን አቅም ለመገንባት የሚያስችል የብድር ስምምነትን መርምሮ በሙሉ ድምፅ አጽድቋል።
የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ እንዳብራሩት፤ ይህ ስምምነት የሕክምና ተቋማትን በዘመናዊ መሣሪያዎችና ግብዓቶች በማደራጀት በዘርፉ የሚታየውን የአቅርቦት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ያለመ ነው።
ይህ ብድር 0.05 በመቶ ዝቅተኛ ወለድ የሚታሰብበት፣ የ15 ዓመት የችሮታ ጊዜ ያለውና በ40 ዓመታት ውስጥ የሚከፈል በመሆኑ ከኢትዮጵያ የብድር ስትራቴጂ ጋር የሚጣጣም መሆኑ ተገልጿል።
የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው የሕክምና መሣሪያዎቹ ከመገዛታቸው በፊት ጥንቃቄ የተሞላበት ጥናት እንዲደረግ፣ የጥገና አገልግሎትና ለምርመራ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች (ሪኤጀንቶች) አብረው እንዲሟሉ አሳስበዋል።
ምክር ቤቱ የቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ መሠረት በማድረግ ረቂቅ አዋጁን በአዋጅ ቁጥር 1406/2018 ማጽደቁን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።