Search

የአየር ንብረት ተጋላጭነትን በመከላከል ጥበብ እየዘመኑ ያሉት የኢትዮጵያ ከተሞች

ረቡዕ መጋቢት 16, 2018 136

21ኛው ክፍለ ዘመን የዓለማችን ገጽታ በከፍተኛ ፍጥነት በከተሜነት እየተቃኘ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ከተሞች 80 በመቶ በላይ የሚሆነውን የሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት (GDP) በማመንጨት የዕድገት ዋና ሞተሮች ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 2025 መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ከዓለማችን 8.2 ቢሊዮን ሕዝብ ውስጥ 45 በመቶ የሚሆነው በከተሞች የሚኖር ነው። ኢትዮጵያም በየዓመቱ 5 በመቶ በሚጠጋ የከተሜነት ዕድገት ፍጥነት በከፍተኛ ሁኔታ እየተነቃቁ ካሉ ሀገራት ተርታ ተሰልፋለች።

ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ከተሞች ዕድገት በአብዛኛው ያልታቀደና ለሥነ-ምህዳር ጥበቃ ትኩረት የማይሰጥ ነበረ። የከተሞቹ ዕድገት በአብዛኛው በተዘበራረቀ መልኩ የሚካሄድ ነበረ።

በአሁኑ ወቅት ግን ከተሞች በመደመር መንግሥት እሳቤ ተቃኝተው ከተሜነትን ከመሠረተ-ልማት ግንባታ ባለፈ የሰውን ልጅ ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያረጋግጥና ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም አካባቢያዊ ሥርዓቶችን የሚያቀናጅ ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤ አድርገው በመመልከት መዋቅራዊ ሽግግር እያካሄዱ ይገኛሉ።  

ይህ ሽግግር ከተሞችን አረንጓዴ ከማድረግ ባለፈ ወደ "ስማርት" (Smart Cities) የመለወጥ ስልታዊ እርምጃ ነው። ዲጂታላይዜሽንን ለአየር ንብረት ጥበቃ እንደ ዋና መሣሪያ በመጠቀም፣ ዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥ በከተሞች እየተስፋፉ ሲሆን፣ ይህም የወረቀት ንክኪን በመቀነስና የትራፊክ ፍሰትን በቴክኖሎጂ በመምራት የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ እያገዘ ነው።

በትክክል የታቀደና ንጹህ የሆነ ከተሜነት ለአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔ እንደሚሆን 2024 የዓለም ከተሞች ሪፖርት ያመላክታል። አንድ ከተማ ንጹህ፣ አረንጓዴና ከሞተር ተሽከርካሪ ውጭ ለሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ምቹ አማራጮችን አካትቶ ሲገነባ የልቀት መጠንን በመቀነስ የአየር ንብረት ተጋላጭነትን የመቋቋም አቅምን ይጨምራል።

ከስማርት ከተሞች ግንባታ ጋር ተያይዞ የፍሳሽ አወጋገድ እና የውኃ አጠቃቀም ሥርዓት ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር ተቆራኝተዋል። ቆሻሻን ወደ ሀብትነት በመቀየር ረገድ የደረቅና የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድን በዲጂታል ካርታ በመደገፍ የብክለት መጠንን የመከታተል ሥራ እየተሠራ ይገኛል።

በውኃ አጠቃቀም ረገድም የብክነት መጠንን ለመቀነስና የውኃ ፍሰትን በዘመናዊ ስማርት ሜትሮች ለመቆጣጠር የሚደረጉ ጥረቶች ከተሞች ለከፍተኛ የአየር ንብረት ቀውስና ለብክለት ሰለባ እንዳይሆኑ ስልታዊ መከላከያ እየሆኑ ነው።

በዚህ ረገድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጀመረው የሸገር ማስዋብና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ለዓመታት ቆሻሻ ይጣልባቸው የነበሩ ወንዞችን በማጽዳትና የፍሳሽ መስመሮችን በማስተካከል ወደ ማራኪ የሕዝብ መዝናኛነት ቀይሯቸዋል።

በአዲስ አበባ የተከናወነው የኮሪደር ልማትም የሞተር እና ሞተር-አልባ ተሽከርካሪዎችን እንዲሁም የሰዎች እንቅስቃሴን በማሻሻል ለአካባቢ ብክለት መቀነስና ለከተማዋ ዲፕሎማሲያዊ ገጽታ መላቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። ይህ ተሞክሮ አሁን ላይ ወደ 75 የኢትዮጵያ ከተሞች ተስፋፍቷል።

እነዚህ ከተሞችም የመንገድ ማሻሻያ፣ የእግርና የብስክሌት መንገዶች ግንባታ እንዲሁም የአረንጓዴ ቦታዎች ልማት በክልል ከተሞችም በስፋት እየተገበሩ ሀገራዊ መነቃቃትን ፈጥረዋል።

ከተሞችን ያማከለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር እና በመላ ኢትዮጵያ የተገነቡት ፓርኮች ከተሜነትን ከሥነ-ምህዳር ጥበቃ ጋር በማጣመር የኢትዮጵያን የቱሪዝም ገጽታ ከፍ አድርገዋል።

እነዚህ ጥረቶች ከተሞችን ለነዋሪዎቻቸው ምቹና ጤናማ ከማድረጋቸውም በላይ፣ ቀጣዩ ትውልድ ንጹህ አየር፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ቀልጣፋ አገልግሎት እና ከተፈጥሮ ጋር የተስማማ ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤ እንዲወርስ በማድረግ ረገድ ታላቅ ትርጉም ይኖራቸዋል።

ኢትዮጵያምን የዓለም ኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል በማድረግ የኢትዮጵያን ገጽታ በበጎ መልኩ ከፍ ከማድረግ ባለፈም ከፍተኛ ውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ እየሆኑ ይገኛሉ።

በለሚ ታደሰ