Search

የቡና ምርትን ለዓለም ገበያ በማቅረብ 43 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል፡- የኦሮሚያ ቡና አምራች ገበሬዎች ሕብረት ስራ ዩኒየን

ሓሙስ መጋቢት 17, 2018 115

የኦሮሚያ ቡና አምራች ገበሬዎች ሕብረት ስራ ዩኒየን ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ውስጥ የቡና ምርት ለዓለም ገበያ በማቅረብ 43 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማስገኘቱን ገለፀ፡፡
የኅብረት ሥራ ዩኒየኑ የምሥረታውን 25ኛ ዓመት በተለያዩ ኩነቶች እያከበረ ይገኛል፡፡
ዩኒየኑ ባለፈው ዓመት ውስጥ 3 ሺህ 700 ሜትሪክ ቶን ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ 27 ሚሊዮን ዶላር፤ባለፉት 6 ወራት 1 ሸህ 728 ሜትሪክ ቶን ቡና በመላክ 16 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ችሏል፡፡
የዩኒየኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ደጀኔ ደዲ እንደገለጹት፣ ተቋሙ ባለፈው ዓመት ብቻ 824 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማስመዝገብ የቻለ ሲሆን ካፒታሉንም ወደ 1.34 ቢሊዮን ብር አሳድጓል፡፡
ባለፉት 25 ዓመታት የመሠረታዊ ማኅበራቱን ቁጥር ከ34 ወደ 413፣ የአባላቱን ቁጥር ደግሞ ከ22 ሺህ ወደ 557 ሺህ በላይ ያሳደገው ዩኒየኑ ምርታማነትን ለማሳደግ ለአርሶ አደሮች ምርጥ የቡና ዝርያዎችን በማቅረብና ቀጣይነት ያለው የቴክኒክ ድጋፍ በመስጠት ረገድ ውጤት ማመዝገቡን ገልፀዋል።
ተቋሙ በአሁኑ ወቅት ምርቱን ወደ "ስፔሻሊቲ" እና "ፕሪሚየም" ደረጃ ለማሸጋገር በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ዩኒየኑ ከቡና ተረፈ ምርት ላይ የካርቦን ፕሮጀክት በመቅረጽ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን እያከናወነ ሲሆን ይህም ለአካባቢው ጥበቃ ከማገዝ ባለፈ ለአርሶ አደሩ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ መፍጠር አስችሎታል።
ዩኒየኑ በቀጣይም ከኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር፣ ጥራቱን የጠበቀ የቡና ምርት ለዓለም ገበያ በማቅረብ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩት እንደሚሰራ አስታውቋል።
በሂሩት እምቢአለ