Search

የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ሉዓላዊነት እያረጋገጠ የሚገኘው "ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ ደማቅ ድሎችን አስመዝግቧል

ዓርብ መጋቢት 25, 2018 77

ከለውጡ ወዲህ በተለይም ባለፉት ሦስት ዓመታት በስፋት ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው የ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ላይ ተጨባጭና ስር ነቀል ለውጦችን በማምጣት የሀገራችንን የማምረት አቅም ወደ አዲስ ምዕራፍ አሸጋግሯል።
ንቅናቄው ፋብሪካዎች ወደ ሥራ እንዲመለሱ፣ የሰው ኃይል እንዲሰባሰብና ምርታማነት እንዲያድግ በማድረግ ረገድ የአንበሳውን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል።
በንቅናቄው ጥረት 325 ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች አዲስ ሥራ የጀመሩ ሲሆን፣ ቀደም ሲል ሥራ አቁመው የነበሩ 830 ኢንዱስትሪዎች ደግሞ ዳግም ወደ ማምረት ተመልሰዋል።
በተጨማሪም ከ1 እስከ 90 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 13 ሸህ 800 አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ መግባታቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
የሀገር ውስጥ ምርቶች የገበያ ድርሻ ከሦስት ዓመት በፊት ከነበረበት 30 በመቶ አሁን ወደ 41 በመቶ አድጓል። ይህም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የመተካት አቅማችን ማደጉን የሚያሳይ ሲሆን፣ ለገቢ ምርቶች ይወጣ የነበረ 3 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሬን ለማዳን አስችሏል።
በተለይም በ2017 የበጀት ዓመት ቀደም ሲል ከውጭ ይገቡ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ተክቶ ወደ ውጭ በመላክ 289 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል። ንቅናቄው በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ከ235 ሸህ 000 በላይ አዳዲስ የሥራ ዕድሎች የፈጠረ ሲሆን፣ በቀጣይም ይህንን ቁጥር ከፍ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት የመከላከያና የፖሊስ የደንብ ልብሶች እንዲሁም የቢራ ገብስ ዘር መቶ በመቶ በሀገር ውስጥ እየተመረቱ ይገኛሉ። ከዚህም ባለፈ የውሃ ቆጣሪዎች፣ ልዩ ልዩ ኬሚካሎች፣ የሕንፃ መሣሪያዎችና አልሚ ምግቦች በስፋት መመረት መጀመራቸው የኢንዱስትሪ ሉዓላዊነታችንን እያረጋገጠ መሆኑን ያሳያል።
መንግሥት የውጭ ጥገኝነትን ለመቀነስ 96 ቁልፍ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማምረት በሰጠው ልዩ ትኩረት፣ የሀገር ውስጥ ምርቶች ተቀባይነት ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል። "ኢትዮጵያ ታምርት" የኢኮኖሚ ነፃነታችንና የብልጽግናችን መሠረት መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል።
የለውጡ ትሩፋት የሆነው የጥራት መንደርም በዓመት ከ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቶን በላይ የገቢና ወጪ ንግድ ምርቶችን ጥራት የማረጋገጥ አስተማማኝ አቅም አለው ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ስለዚህ የጥራት መንደር "ይህ ወሳኝ ተቋም የሀገር ውስጥ ምርቶቻችን በዓለም ገበያ የሚኖራቸውን ተወዳዳሪነት በማላቅ በዓለም የእሴት ሰንሰለት የሚኖራቸውን ተሳትፎ የሚያጎለብት ነው" ማለታቸው ይታወሳል።
በመሀመድ ፊጣሞ