Search

ማንሰን ኢንቨስትመንትስ ጥራት ያላቸው የሴራሚክ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለማስመረት እና ለማከፋፈል ስልታዊ ስምምነት ተፈራረመ

ቅዳሜ መጋቢት 26, 2018 79

ማንሰን ኢንቨስትመንትስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ለኢትዮጵያ ገበያ ተስማሚ የሆኑ፣ ጥራት ያላቸው እና በልዩ ሁኔታ ዲዛይን የተደረጉ የሴራሚክ እና የፖርስሊን ምርቶችን በኢትዮጵያ ለማስመረት እና ለማከፋፈል የሚያስችለውን ስትራቴጂያዊ ስምምነት ከቻይናው ባይጂያ የሴራሚክ አምራች ድርጅት ጋር ተፈራርሟል።
በፊርማው ሥነ-ሥርዓት ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና የንግድ ማኅበረሰብ አባላት ተገኝተዋል።
ከአዲስ አበባ በ65 ኪ.ሜ ርቀት በሚገኝ ቱለፋ በተባለ ቦታ የሚገኘው የባይጂያ ፋብሪካ፣ ከ50 ሚሊዮን ዶላር በሚበልጥ ኢንቨስትመንት የተገነባ ሲሆን፣ በዓመት 14 ሚሊዮን ካሬ ሜትር የሚሸፍኑ ምርቶችን የማምረት አቅም አለው።
ይህም ፋብሪካውን በኢትዮጵያ ግዙፉ የሴራሚክ አምራች ድርጅት ያደርገዋል።
ድርጅቱ የኢትዮጵያን ዓመታዊ የሴራሚክ ምርት ፍላጎት 70 በመቶ በመሸፈን፣ ምርቱን ከውጭ ሀገራት ለማስገባት የሚወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ያስቀራል።
ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት “ኢትዮጵያ ታምርት” በሚል መሪ ሐሳብ የሀገር ውስጥ ምርቶችን ለማስፋፋት ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ትልቅ ሚና ይጫወታል።
የማንሰን ኢንቨስትመንትስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዳዊት እርገቱ የአጋርነት ስምምነቱን አስመልክቶ እንዳሉት፣ “ይህ አጋርነት ማንሰን ጥራት ያላቸው እና በገበያ ፍላጎት ላይ የተመሠረቱ ምርቶችን በተቀናጀ የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪ ትብብር ለኢትዮጵያ ለማቅረብ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል”።
የባይጂያ ሴራሚክ ማኑፋክቸሪንግ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ጃንግ ሁዋ በበኩላቸው፣ ይህ ትብብር በኢትዮጵያ እያደገ ያለውን ፍላጎት ማሟላት የሚያስችሉ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶችን ለማቅረብ ጠንካራ መሠረት እንደሚጥል ገልጸዋል።
ማንሰን ኢንቨስትመንትስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ በሀገራችን የመጀመሪያ እና ተጠቃሽ በሆኑት አራዳ ሞል እና ምናብ ዌልነስ ክለብ ኢንቨስትመንቶቹ የሚታወቅ የኩባንያዎች ቡድን አባል ነው።
 
በወንድወሰን አፈወርቅ