ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት መሠረታዊና ታሪካዊ የተባለ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሽግግር በማድረግ ላይ ትገኛለች። ሀገራችን ለረጅም ዓመታት ስትከተለው የነበረውንና መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊ የነበረበትን "ልማታዊ መንግሥት" ሞዴል በመተው፣ ወደ ግል ዘርፍ መራሽና ገበያ መር የኢኮኖሚ ሥርዓት ተሻግራለች።
ይህ ሽግግር በዋነኝነት "ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ" በሚል መዋቅራዊ ሪፎርም የሚመራ ሲሆን፣ ዋና ዓላማውም ለዘመናት የቆዩ የኢኮኖሚ መዛባቶችን በማስተካከል ዘላቂ ብልጽግናን ማረጋገጥና የዜጎችን ተጠቃሚነት ማሳደግ ነው፡፡
ቀደም ሲል የነበረው የኢኮኖሚ ሞዴል መንግሥት በኢኮኖሚው ውስጥ ሰፊ ጣልቃ ገብነት እንዲኖረው የሚያደርግና የግል ዘርፉን ሚና የሚገድብ ነበር።
በተለይም በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች ወቅት መንግሥት የኢኮኖሚው ዋና አንቀሳቃሽ በመሆን ግዙፍ መሠረተ ልማቶችን በበጀትና በብድር ሲያከናውን ቆይቷል። በዚህም ምክንያት እንደ ቴሌኮም፣ አየር መንገድና ባንክ ያሉ ስትራቴጂካዊ ዘርፎች ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ቁጥጥር ስር ነበሩ።
ከዚህም ባለፈ መንግሥት ለግዙፍ ፕሮጀክቶች ዝቅተኛ ወለድ ያለው ብድር ለማቅረብ ሲል የፋይናንስ ዘርፉን በጥብቅ ይቆጣጠር ነበር። ለምሳሌ የግል ባንኮች ከሚሰጡት ብድር 27 በመቶውን የብሔራዊ ባንክ ቦንድ እንዲገዙ መገደዳቸው ለግል ዘርፉ የሚቀርበውን የፋይናንስ አቅርቦት በእጅጉ አጥብቦት መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡
ይህንን አካሄድ በመቀየር ረገድ የአሁኑ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አዲስና ውጤታማ አቅጣጫዎችን ይዞ መጥቷል። የግል ዘርፉን የኢኮኖሚው ሞተር ለማድረግ የታለመው ይህ ሪፎርም፣ የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያን፣ የዘርፍ ነጻነትንና የመንግሥት የንግድ ተቋማትን ወደ ግል ማዛወርን እንደ ትልቅ ስኬት ይቆጥራል።
ደፋር እርምጃ የተባለለት የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያው የብር ዋጋ በገበያ እንዲወሰን በማድረግ፣ ለዓመታት የኢኮኖሚው ፈተና የነበረውን ጥቁር ገበያ ለማጥፋትና ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ትልቅ በር ከፍቷል።
በተጨማሪም የዋጋ ግሽበትን በዘላቂነት ለመቀነስ የመንግሥት የብድር ፍላጎት ከብሔራዊ ባንክ እንዳይሆን ተደርጎ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡
ሌላው የለውጡ መገለጫ ቀደም ሲል በመንግሥት ብቻ ተይዘው የነበሩ ዘርፎች ለግል ባለሀብቶች ክፍት መደረጋቸው ነው። የኢትዮ ቴሌኮም በከፊል ወደ ግል መዛወር፣ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ወደ ገበያ መግባት፣ የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ እንዲሠሩ መፈቀዱ እና የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ መመሥረት የሪፎርሙ ውጤታማነት ማሳያዎች ናቸው።
እነዚህ እርምጃዎች በዘርፉ የውድድር መንፈስን ከመፍጠራቸውም በላይ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የሥራ ዕድል እንዲሰፋ በማድረግ ረገድ የጎላ ድርሻ አላቸው፡፡
በተጨማሪም መንግሥት ከአስፈጻሚነትና ከንግድ ተፎካካሪነት በመውጣት ወደ አመቻችነት ሚናው ተመልሷል። ንግድ የመሥራት ምቹነትን ለማሻሻል ትኩረት በመስጠት ለግብርና (በተለይ የበጋ ስንዴ)፣ ለማዕድን፣ ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለቱሪዝም እና ለአይሲቲ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ላይ ይገኛል።
በተለይም በበጋ ስንዴ ልማት የተመዘገበው ስኬት ሀገራችን በምግብ ራስን ለመቻል ለምታደርገው ጥረት ትልቅ ማሳያ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሽግግር ሀገራችንን ካለፈው የተዘጋና በመንግሥት ቁጥጥር ስር ከነበረ ሥርዓት አውጥቶ ለዓለም አቀፍ ውድድርና ለግል ዘርፍ ዕድገት ዝግጁ እያደረጋት ነው።
ምንም እንኳን እንደ የዋጋ ግሽበት ያሉ የሽግግር ወቅት ፈተናዎች ቢኖሩም፣ ማሻሻያዎቹ በረጅም ጊዜ አስተማማኝ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ያላቸው ፋይዳ የላቀ ነው።
ይህም ኢትዮጵያን በምሥራቅ አፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ የኢኮኖሚ ኃይል የማድረግ ራዕይ ስኬታማ መሆኑን ያበስራል፡፡
በሃይማኖት ከበደ