የሀገራት ተወካዮችና የድርጅት መሪዎች ለስብሰባና ለንግድ ትርዒት ከሀገር ሀገር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ "ኮንፍረንስ ቱሪዝም" ወይም "ማይስ ቱሪዝም" ይባላል።
እንዲህ ያሉ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን ማዘጋጀት የውጭ ምንዛሪ ገቢን ከመጨመር ባለፈ ንግድና ኢንቨስትመንትን በመሳብ ለሆቴሎች፣ ለትራንስፖርትና ለሀገር ውስጥ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሾች ትልቅ እገዛ ያደርጋል።
ዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆንና አቅምን ለማሳየት የቪዛ አገልግሎት መዘመንን፣ የሆቴሎች ብቃትና የቴክኖሎጂ ዝግጅትን ይጠይቃል።
በዚህ ረገድ ቀደም ሲል የመሸጋገሪያ ከተማ የነበረችው አዲስ አበባ አሁን ላይ በሙዚየሞች፣ በኮንፍረንስ ማዕከላትና በኮሪደር ልማት ሥራዎች ራሷን የቻለች የቱሪስት መዳረሻ መሆን ችላለች።
ኢትዮጵያ በ2017 በጀት ዓመት ከ150 በላይ፣ በ2018 የመጀመሪያ ሥድስት ወራት ደግሞ ከ100 በላይ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን ማስተናገዷን የቱሪዝም ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።
የአፍሪካ ኅብረት መናገሻና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ መሆኗ ለዘርፉ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፣ የመደመር መንግሥትም መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት የሥራ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል።
የዘርፉ ባለሙያዎች ኢትዮጵያ የ"ማይስ ቱሪዝም" ማዕከል እንድትሆን የመሰረተ ልማት አቅምን ማሳደግ፣ የሰው ኃይልን ማሰልጠንና ሁነቶችን በዘመናዊ መንገድ ማዘጋጀት እንደሚገባ ይመክራሉ።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፉ ቀን ከሌት በመስራት ራሷን በአዲስ መልክ ለዓለም እየገለጠች ትገኛለች።
በመቅደላዊት ደረጀ