Search

ከዝናብ ጥገኝነት ወደ ምግብ ሉዓላዊነት፡ የኢትዮጵያ የመስኖ ልማት አዲስ ምዕራፍ

ሰኞ መጋቢት 28, 2018 227

ኢትዮጵያ ለዘመናት የዘለቀውን የዝናብ ጥገኝነት በመቀየር ግብርናዋን በመስኖ ላይ የተመሠረተ ለማድረግ የጀመረችው ስትራቴጂያዊ ሽግግር ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል።

ይህ እንቅስቃሴ በዋነኝነት የሀገራችንን ግብርና ከአየር ንብረት ተለዋዋጭነት በማላቀቅ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተቀረጸውን የዐሥር ዓመቱን መሪ የልማት ዕቅድ (2013 - 2022 .) መሠረት ያደረገ ነው።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተከናወኑ ግዙፍ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታና የጥቃቅን መስኖ ማስፋፋት ሥራዎች ሀገራችን በምግብ ራሷን ለመቻል ለያዘችው ግብ እንደ ዋነኛ ምሰሶ እየታዩ ሲሆን፣ በተለይም 2017 እና 2018 . የታዩት ክንውኖች ኢትዮጵያ ዓመቱን ሙሉ ወደ ማምረት መሸጋገሯን በተጨባጭ ማሳያ ናቸው።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚገነቡ ግዙፍ የመስኖ ግድቦች ለአምራች ዘርፉ አዲስ ተስፋን ሰንቀዋል። ለዓመታት ተቋርጦ የነበረውና በቅርቡ ተመርቆ ወደ ሙሉ ሥራ የገባው 60 ሺህ ሄክታር የመልማት አቅም ያለው የተንዳሆ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ለአፋር ክልል አርብቶ አደሮች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ለእንስሳት መኖና ለምግብ ዋስትና ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

በተመሳሳይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ልዩ ክትትል ወደ ሥራ ተመልሶ በዚህ በጀት ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው የመገጭ ግድብ፣ 30 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ከማድረጉም በላይ የጎንደርን ከተማ የውኃ ጥም የሚቆርጥ በመሆኑ ልዩ ትርጉም ይሰጠዋል።

እነዚህና በኦሮሚያ ክልል 6 ቢሊዮን ብር ወጪ ተገንብቶ 20 ሺህ አባወራዎችን ተጠቃሚ ያደረገው የወልመል ወንዝ መስኖ ፕሮጀክት፣ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ልዩ ትኩረትና የታየውን የግንባታ ፍጥነት ያሳያሉ።

የመስኖ ልማቱ ያመጣው ትልቁ ስኬት በስንዴ ምርታማነት ላይ የታየው ተዓምራዊ ለውጥ ነው። ኢትዮጵያ 2017 . የምርት ዘመን በዝናብና በመስኖ በድምሩ 280 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስንዴ ማምረት የቻለች ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 128 ሚሊዮን ኩንታሉ 3.5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ በመስኖ የለማ ነው።

ይህ ውጤት ሀገራችን በየዓመቱ ለስንዴ ግዢ ታወጣው የነበረውን አንድ ቢሊዮን ዶላር ገደማ የውጭ ምንዛሬ ለማዳን አስችሏታል።

ይህ የስኬት ጉዞ በወለጋ በቄጦና በአርጆ ዲዴሳ ፕሮጀክቶች አማካኝነት ተጠናክሮ ቀጥሏል። በቄለም ወለጋ የተሠራው የቄጦ ግድብ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ወደ ሥራ ገብቷል። እነዚህ ግድቦች በሙሉ አቅማቸው ወደ ሥራ ሲገቡ በቆሎና የቅባት እህሎችን በዓመት ሦስት ጊዜ ለማምረት በሚደረገው ጥረት የሚያሳኩ ይሆናል።

በሶማሌ ክልል የዋቢ ሸበሌን ወንዝ በመጥለፍ የጎዴና ቃላፎ ፕሮጀክቶችን ወደ ልማት በማስገባት ተችሏል። እነዚህ በቆላማ አካባቢዎች የሚገኙ ፕሮጀክቶች ማኅበረሰቡን ከአርብቶ አደርነት ወደ ከፊል አርሶ አደርነት በማሸጋገር ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ አላቸው።

ከግዙፍ ፕሮጀክቶች ጎን ለጎን የጥቃቅን መስኖ ልማት በአርሶ አደሩ የኑሮ ደረጃና የአመጋገብ ባህል ላይ መሠረታዊ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ።

የመስኖ ተጠቃሚ የሆኑ አርሶ አደሮች ዓመታዊ ገቢያቸው በአማካይ 55 በመቶ ማደጉን ተጨባጭ ማስረጃዎች ይጠቁማሉ።

በቀጣይ ዓመታትም የፀሐይ ኃይል የሚሠሩ የውኃ ፓምፖችን በስፋት በማቅረብና የኩታ ገጠም እርሻ ዘዴን ከመስኖ ጋር በማቀናጀት ግብርናውን በቴክኖሎጂ ለማዘመን ታቅዷል።

ይህ በመስኖ ዘርፍ እየታየ ያለው መነቃቃትና የመሠረተ ልማቶች በጥራትና ፍጥነት መጠናቀቅ ኢትዮጵያን በምግብ ራሷን የቻለችና ምርቶቿን ለዓለም ገበያ የምታቀርብ ሀገር ለማድረግ እየተከናወነ ያለውን ታሪካዊ ሽግግር የሚያረጋግጥ ነው።

ይሁን እንጂ ይህ ተስፋ ሰጪ ሽግግር ይበልጥ ስኬታማ እንዲሆን አሁንም ድረስ መፈታት የሚገባቸው ዘርፈ-ብዙ ተግዳሮቶች አሉ። በዲዛይንና ጥናት ግድፈቶች የሚፈጠሩ የግንባታ መዘግየቶች፣ የዘላቂ ጥገና ሥርዓትና የፋይናንስ እጥረት፣ እንዲሁም የቦዮች በደለል መሞላት የመሠረተ ልማቶቹን ዕድሜ እያሳጠሩት ይገኛሉ።

ከዚህም በተጨማሪ የተቋማት የአስተዳደር ክፍተት፣ በአርሶ አደሩ ዘንድ ያለው የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የውኃ አስተዳደር ክህሎት ውስንነት፣ እንዲሁም የተስተካከለ የገበያ ትስስርና የግብዓት አቅርቦት ችግሮች ሌሎች የዘርፉ ማነቆዎች ናቸው።

በመሆኑም ሀገራችን የጀመረችውን የምግብ ሉዓላዊነት የማረጋገጥ ስትራቴጂያዊ ግብ ከዳር ለማድረስ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ከመገንባት ጎን ለጎን እነዚህን የጥገና፣ የአቅም ግንባታ እና የገበያ ትስስር ፈተናዎች በዘላቂነት መቅረፍ ወሳኝ ተግባር ይሆናል።

በለሚ ታደሰ