መንግሥት ተግባራዊ ያደረገው ስር ነቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም በማዕድን ዘርፉ ላይ መሬት የወረዱ ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገበ ይገኛል።
ቀደም ሲል በዓመት 13 ቶን ብቻ የነበረው የወርቅ ምርት በአሁኑ ወቅት ወደ 39 ቶን ከፍ ማለቱ የሪፎርሙ ቀጥተኛ ውጤት ሲሆን፣ ይህም ከዘርፉ ይገኝ የነበረውን የ300 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ወደ 3.5 ቢሊዮን ዶላር በማሳደግ ታሪካዊ ስኬት አስመዝግቧል።
ይህ አስደናቂ ለውጥ ከባንክ ሥርዓት ውጪ ይባክን የነበረው የሀገር ሀብት ወደ ማዕከላዊ የፋይናንስ ሥርዓት መግባቱን በግልጽ ያሳያል።
ከወርቅ በተጨማሪም "የዓለማችን አዲሱ ነዳጅ" ተብለው የሚጠሩት እንደ ሊቲየም እና ታንታለም ያሉ ለዘመናዊ ባትሪ ግብዓት የሚውሉ ማዕድናት እሴት ተጨምሮባቸው ለገበያ እንዲቀርቡ በመደረጉ የውጭ ምንዛሬ ገቢ እያስገኙ ነው።
በተመሳሳይ በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል የሚገኘው የፖታሽ ክምችት የግብርናው ዘርፍ የጀርባ አጥንት ከመሆኑ ባለፈ፣ ኢትዮጵያን ከውጭ ማዳበሪያ ጥገኝነት የሚያላቅቅና ለቀጠናው ሀገራትም ተስፋ የሚሰጥ ታላቅ የኢኮኖሚ ምንጭ ነው።
የማዕድን ሚኒስቴር ዘርፉን ለማዘመንና ተጠያቂነትን ለማስፈን ሦስት ዋና ዋና ስትራቴጂዎችን ተግባራዊ አድርጓል።
በዚህም ባህላዊ ማዕድን አውጪዎችን በዲጂታል መታወቂያ በማደራጀት ወደ ሕጋዊ ሥርዓት ማምጣት፣ የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን በማስቀረት የዲጂታል ግብይትን መዘርጋት እንዲሁም በሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) የታገዘ የመረጃ ክትትል በማድረግ የምርት መቀነስንና ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴን አስቀድሞ መተንበይ የሚያስችል ሥርዓት መገንባት ተችሏል።
እንደ ብረት እና መዳብ ያሉ ተፈጥሯዊ ጸጋዎች ላይ ትኩረት በመደረጉም የሀገሪቱን የኢንዱስትሪ ፍላጎት በራስ አቅም ለመሸፈን ሰፊ ጥረት እየተደረገ ሲሆን፣ ይህም በማዳበሪያ፣ በሲሚንቶ እና የነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ ላይ ለበርካታ ዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል።
በአጠቃላይ በማዕድን ዘርፉ እየታየ ያለው ይህ ኢኮኖሚያዊ ሽግግር የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ከመሠረቱ የሚቀይር ነው።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ