በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴ የሚመራው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ለኢትዮጵያ የተቀናጀ የሦስትዮሽ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ድጋፍ ላይ ውይይቶችን ለማካሄድ ከዓለም ባንክ እና ከጣሊያን ልዑካን ቡድን ተወካዮች በከፍተኛ አመራሮች ደረጃ ውይይት አድርጓል።
መድረኩ ያተኮረው የኢትዮጵያን ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ለመደገፍ እና ኢትዮጵያ ቅድሚያ ከሰጠቻቸው የልማት ዕቅዶች እና ዘርፎች ጋር የሚጣጣም ወቅታዊ እና ሊገመት የሚችል ፋይናንስ ለማንቀሳቀስ በሦስቱ አጋሮች መካከል ያለውን ትብብር በማጠናከር ላይ ነው።
የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የቅርብ ጊዜውን የማክሮ ኢኮኖሚ ዕድገት አጉልቶ በማሳየት የለውጥ ፍጥነትን ለማስቀጠል፣ የፊስካል ዲሲፕሊንን ለማሻሻል እና ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገትን አጠናክሮ ለማስቀጠል ያለውን ጠንካራ ቁርጠኝነት አረጋግጧል።
ውይይቶቹ ተጽዕኖን ከፍ ለማድረግ እና በኢትዮጵያ ቀልጣፋ የሀብት አጠቃቀምን ለማረጋገጥ ከልማት አጋሮች የተጣጣመ ድጋፍ አስፈላጊነት ላይ አፅንዖት ሰጥተዋል።
የሦስትዮሽ ውይይቱ አካላት ኢትዮጵያ ውስብስብ በሆነው ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ አካባቢ ውስጥ ዕድገቷን አስቀጥላ እንድትጓዝ በመርዳት የሀገር ውስጥ የሪፎርም አጀንዳ የሚያጠናክር የተቀናጀ የበጀት ድጋፍ ለማቅረብ የሚያስችሉ ዘዴዎች በውይይቱ ወቅት ተዳስሰዋል።
የጣሊያን ልዑካን ቡድን በተለይም የሁለትዮሽ ትብብርን በማሻሻል እና ከባለብዙ ወገን የፋይናንስ ማዕቀፎች ጋር በማጣጣም የኢትዮጵያን የልማት ጥረቶች ለመደገፍ ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጧል። የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የማሻሻያ ፕሮግራም ቀጣይነት ያለው እና ውጤታማ የፋይናንስ ድጋፍን ለማሳደግ ከአጋሮች ጋር በቅርበት ለመሥራት ያለውን ዝግጁነት አረጋግጧል።
ሁሉም ወገኖች ጠንካራ አጋርነት ማጠናከር አሁን ያሉትን ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ችግሮች፣ ውጫዊ ድንጋጤዎች፣ የፋይናንስ ገደቦች እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ጨምሮ በመፍታት ረገድ ያለውን ወሳኝ ሚና የጋራ መረዳት ላይ ደርሰዋል።
ዘላቂ ተሳትፎ፣ የፖሊሲ ቅንጅት እና የጋራ ኃላፊነትን በመወጣት ውጤታማ የልማት ስኬቶችን በማምጣት ረገድ ያለውን ጠቀሜታ አፅንዖት መስጠታቸውን በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል።
ውይይቱ ትብብርን የበለጠ ለማጠናከር እና የተቀናጀ የበጀት ድጋፍ ማዕቀፍ ለማጠናቀቅ የሚደረገውን ጥረት ለማፋጠን በጋራ መግባባት ተጠናቅቋል።
ኢትዮጵያ ችግሮችን ተቋቁማ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ተከታታይነት ያለው ዕድገት በማስመዝገብ እና ወሳኝ የሆኑ መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን በማድረግ ጤናማ የማክሮ ኢኮኖሚ አስተዳደርን ለማስጠበቅ ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ ገልጻለች።