ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ነፃ ንግድ ቀጣና ማደጋቸው፣ ከምርት ተግባር ባለፈ የንግድ እና የሎጀስቲክስ ሥርዓቱን በማዘመን ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚኖራቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ቀደም ሲል ትኩረታቸው በአምራች ዘርፍ ላይ ብቻ የነበረ ቢሆንም፣ ወደ ነፃ ንግድ ቀጣና ሲቀየሩ ግን የንግድ እንቅስቃሴን የማሳለጥ ሰፊ አቅም ይኖራቸዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ፤ የነፃ ንግድ ቀጣናዎች ዋነኛ ፋይዳ ኢትዮጵያ የባሕር በር የሌላት መሆኑ የሚያስከትልባትን ተግዳሮት ለመቅረፍ እና የሎጀስቲክስ ወጪን በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ ማስቻሉ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደ ዱባይ ያሉ ሀገራት የነፃ ንግድ ቀጣናዎችን ተሞክሮ በመጥቀስ፣ ሀገራቱ ቀጣናዎቹን ለዓለም አቀፍ ምርቶች ዳግም ወጪ ንግድ (Re-export) መድረክነት እንደሚጠቀሙባቸው አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ ቀዳሚ ዓላማ ግን ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶች በተቀላጠፈ የሎጀስቲክስ ሥርዓት እንዲገቡ እና ለሀገር ውስጥ ገበያ በቅናሽ ዋጋ እንዲቀረቡ ለማድረግ መሆኑን አብራርተዋል።

በአርአያነት የተጠቀሰው የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጣና ከተመሠረተ ጥቂት ወራት ቢሆኑትም፣ ባለፉት ወራት ብቻ በቀጣናው ከ27 ሚሊዮን ዶላር በላይ የንግድ ግብይት መከናወኑን ይፋ አድርገዋል።
ይህ ውጤት የተገኘው በንግድ ዘርፍ ብቻ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ቀጣናው ከደረቅ ወደቦች ጋር ተቀናጅቶ ሲሠራ የሀገራችንን ኢኮኖሚያዊ አቅም ይበልጥ እንደሚያሳድገው ጠቁመዋል።
በአጠቃላይ የነፃ ንግድ ቀጣናዎች ከወጪ ንግድ ባለፈ የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ተገልጿል።
ንፍታሌም እንግዳወርቅ