የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) እ.ኤ.አ በ2026 ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራትን የኢኮኖሚ ዕድገት አስመልክቶ ያወጣው ትንበያ፣ ኢትዮጵያ 9.2 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ ቀጣናውን እንደምትመራ አረጋግጧል። በመካከለኛው ምሥራቅ ካለው የጂኦፖለቲካዊ ውጥረት እና የዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ መዋዠቅ አንፃር ሲታይ፣ ይህ ዕድገት በአጋጣሚ የተገኘ ሳይሆን ሀገራችን ባለፉት ዓመታት የተገበረቻቸው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የመደመር ፍልስፍና ያመጡት ተጨባጭ ውጤት ነው።
1. የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም እና የፋይናንስ ሉዓላዊነት
የኢትዮጵያ መዋቅራዊ ለውጥ መሠረት የተጣለው በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ በተወሰዱ ደፋር እርምጃዎች ነው። ከዚህ ቀደም የነበረው መዛባት የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የዋጋ ንረት እና የዕዳ ጫናን አስከትሎ ቆይቷል።
በሐምሌ 2024 የተተገበረው በገበያ የሚመራ የውጭ ምንዛሬ ተመን፣ ለዘመናት የቆየውን ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ከመግታቱም በላይ የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን እና የሐዋላ ፍሰትን በከፍተኛ ሁኔታ አሳድጓል።
መንግሥት የንግድ ብድሮችን በመተው እና ከኦፊሴላዊ አበዳሪዎች ኮሚቴ (OCC) ጋር የ3.5 ቢሊዮን ዶላር የዕዳ ሽግሽግ ስምምነት ላይ በመድረሱ፣ ባለፉት ሰባት ዓመታት 12.7 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ዕዳ መክፈል ተችሏል። ይህም ሀገራችን ከዕዳ ጫና አላቅቆ ለልማት የሚውል የፋይናንስ አቅም ፈጥሯል።
2. መዋቅራዊ ለውጥ በምርት ዘርፎች (Structural Transformation)
የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ማለት የሰው ኃይል እና ሀብት ከዝቅተኛ ምርታማነት ወደ ከፍተኛ ምርታማነት የሚሸጋገርበት ሂደት ነው። ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ትልቅ እምርታ አሳይታለች።
ስንዴን ከውጭ ከመግዛት ወደ ላኪነት የተደረገው ሽግግር ዋነኛው ስኬት ነው። በስንዴ የመጣው ስኬት ዕድገቱን ቀጥሎ በ2018 የመጀመሪያ ስድስት ወራት ብቻ 126.69 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ መመረቱ የኩታ ገጠም እርሻ እና የበጋ መስኖ ልማት ውጤታማነት ማሳያ ነው።
አሁንም ዋነኛ የወጪ ምንዛሬ ማግኛ የሆነው ቡና በ2017 በጀት ዓመት 11.4 ሚሊዮን ኩንታል ተመርቷል። በሌማት ትሩፋትም የወተት ምርት፣ የዕንቁላል እና የስጋ ምርቶች ዕድገት የዜጎችን ሥነ-ምግብ ከማሻሻል ባለፈ ግብርናውን የንግድ እና የኢንዱስትሪ ግብዓት አድርጎታል።
“ኢትዮጵያ ታምርት” እና የማኑፋክቸሪንግ መነቃቃት
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ አቅም አጠቃቀም ከ46 በመቶ ወደ 65.02 በመቶ አድጓል። እንደ ቢራ ብቅል፣ የምግብ ዘይት፣ ስማርት ፖሎች እና ትራንስፎርመሮች የመሳሰሉ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት በ2017 ብቻ 4.5 ቢሊዮን ዶላር ማዳን ተችሏል።
ነፃ የኢኮኖሚ ዞኖች መስፋፋት ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳቢያ እና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ምቹ ምኅዳር ፈጥረዋል።
የማዕድን ዘርፍ፡ አዲሱ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት
ዘርፉን ወደ መደበኛ ሥርዓት በማስገባት አስደናቂ የውጭ ምንዛሬ ማመንጨት ተችሏል። በ2012 በጀት ዓመት 3.3 ቶን የነበረው የወርቅ ንግድ፣ በ2017 ወደ 38.83 ቶን ከፍ ብሏል። በዚህም ከወርቅ የሚገኘው ገቢ ከ200 ሚሊዮን ዶላር ወደ 3.46 ቢሊዮን ዶላር አድጓል። ይህም የኮንትሮባንድ መንገዶችን በቴክኖሎጂ በመዝጋት የተገኘ መዋቅራዊ ለውጥ ነው።
3. ዲጂታል ኢኮኖሚ እና ዘመናዊ የአገልግሎት ዘርፍ
ኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን እንደ ኢኮኖሚ ማሳለጫ እየተጠቀመችበት ትገኛለች።
የ"ፋይዳ" ብሔራዊ መታወቂያ ከ41 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን መድረሱ፣ እንዲሁም በ2017 በጀት ዓመት 16 ትሪሊዮን ብር በዲጂታል የክፍያ ሥርዓት መዘዋወሩ የፋይናንስ አካታችነትን አረጋግጧል።
የ"5 ሚሊዮን ኮደርስ" መርሐ-ግብር እና የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ማዕከል መቋቋም፣ ሀገራችን ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ዕውቀት መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የሚደረግ ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንት ነው።
4. ሜጋ ፕሮጀክቶች፣ ቱሪዝም እና የኢነርጂ ሉዓላዊነት
"ገበታ ለሀገር/ሸገር/ትውልድ" ፕሮጀክቶች የሀገር ገጽታን በመቀየር በ2017 የቱሪስት ፍሰቱን ወደ 1.3 ሚሊዮን አሳድገዋል። ይህ የትርክት ግንባታ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ በመሆን እያገለገለ ነው።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ሀገራዊ የኃይል አቅምን ወደ 10 ሺህ ሜጋ ዋት ያሳደገ ሲሆን፣ የኮሪደር ልማቱ ከተሞችን ለነዋሪዎች ምቹ ከማድረግ ባለፈ ዘመናዊ የኢኮኖሚ ማዕከላት አድርጓቸዋል።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የ2026 ትንበያ የኢትዮጵያን ትክክለኛ የዕድገት አቅጣጫ ያረጋገጠ ነው። በአየር ንብረት ለውጥ፣ በዓለም አቀፍ የጂኦፖለቲካዊ መፋጠጦች፣ እንዲሁም በሀገር ውስጥ ተግዳሮቶች መሀል የተመዘገበው ይህ ባለ 9.2 በመቶ ዕድገት፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያለውን የመቋቋም አቅም (Resilience) በግልጽ ያሳያል።
በብሪክስ አባልነት የተፈጠረው አዲስ የኢኮኖሚ ትስስር 13.1 ቢሊዮን ዶላር ያወጡ እንደ ሚንግ ያንግ ስማርት ኢነርጂ ያሉ ታላላቅ የውጭ ኢንቨስትመንቶች፣ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ እያስመዘገበ ያለው ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ኢትዮጵያን በ2022 ዓ.ም የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕይን እውን የሚያደርጉ ናቸው።
መንግሥት የዋጋ ንረትን ወደ ነጠላ አሃዝ ለማውረድ እና የዲጂታል ኢኮኖሚውን ለማስፋፋት የያዘው ግብ ከተሳካ፣ በ2038 ዓ.ም ከዓለም 10 ግዙፍ ኢኮኖሚዎች ተርታ ለመሰለፍ የተቀመጠው ግብ ሊደረስበት የሚችል ተጨባጭ ዕቅድ መሆኑን የኢኮኖሚው የአሁኑ አፈጻጸም ያረጋግጣል።
በአዶኒያስ ወደልደአረጋይ