ኢትዮጵያ የጀመረችው ሁለንተናዊ የሪፎርም ጉዞ ተጨባጭ ፍሬዎችን እያፈራ፣ የሀገራችን የብልጽግና ምሶሶዎች በፅኑ መሠረት ላይ እየተከለ ይገኛል። የ2018 በጀት ዓመት የሦስተኛው 100 ቀን አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያመላክተው፣ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች አስደናቂ እምርታዎችን እያስመዘገበች መሆኑን ነው።
ባለፉት ስምንት ዓመታት በአማካይ የ7.5 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ስታስመዘግብ የቆየችው ኢትዮጵያ፣ በ2018 በጀት ዓመት የ10.2 በመቶ ድርብ አሃዝ ዕድገት ለማስመዝገብ በልበ ሙሉነት እየተጓዘች ነው። ይህ ዕድገት በመለኪያ ቁጥሮች ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን፣ መሰረተ-ሰፊና አካታች መሆኑ ልዩ ያደርገዋል።
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የነበሩባቸውን የኪሳራ ጠባሳዎች አሽረው ወደ ላቀ ትርፋማነት ተሸጋግረዋል። በ2010 ዓ.ም የ8 ቢሊዮን ብር ኪሳራ ያስመዘገቡት እነዚህ ተቋማት፣ በ2018 ዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ 351 ቢሊዮን ብር (ከታክስ በፊት) ትርፍ ማግኘታቸው የሪፎርሙን ስኬታማነት በጉልህ ያሳያል። በተመሳሳይ፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በዘጠኝ ወራት ውስጥ 3.52 ቢሊዮን ዶላር ሲመዘግብ፣ 13 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ አዳዲስ ስምምነቶች ተፈርመዋል። ይህም ለ4.32 ሚሊዮን ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠር ምክንያት ሆኗል።
የኢትዮጵያ ግብርና ከባህላዊ አሰራር ወጥቶ ወደ ዘመናዊ መዋቅራዊ ሽግግር እያመራ መሆኑ በተለያዩ መሳያዎች የሚገለፅ ሆኗል፡፡ ከ2010 እስከ 2017 ባለው ጊዜ ውስጥ የትራክተር አጠቃቀም በ476.9 በመቶ፣ የኮምባይነር አጠቃቀም ደግሞ በ2487.6 በመቶ ማደጉ ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት ያሳያል።
የግብርና ሜካናይዜሽን የሰብል ምርታማነትን በከፍተኛ ሁኔታ አሳድጎታል። በ2018 ዘጠኝ ወራት የተሰበሰበው 236.29 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት፣ ከ2010 እስከ 2017 ከነበረው ምርት ጋር ሲነጻጸር የ173 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። የ"ሌማት ትሩፋት" መርሐ ግብርም የእንቁላል ምርትን በ369 በመቶ፣ የወተት ምርትን በ143 በመቶ እንዲሁም የማር ምርትን በ509.5 በመቶ በማሳደግ የዜጎችን ሥርአተ-ምግብ በመሰረቱ እቀየረው ይገኛል፡፡ ለአካባቢ ጥበቃ በተሰጠው ትኩረትም የሀገራችን የደን ሽፋን 23.6 በመቶ ደርሷል።
"ኢትዮጵያ ታምርት" ሀገራዊ ንቅናቄ የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ወደ 46 በመቶ ከፍ በማድረጉ፣ የሀገር ውስጥ ምርቶች የገበያ ድርሻቸው 66 በመቶ ደርሷል። ይህም በዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ 4.9 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬን ለማዳን አስችሏል። ከዚህም በላይ በተለያዩ ችግሮች ተዘግተው የነበሩ 993 ፋብሪካዎች ዳግም ወደ ስራ ተመልሰዋል።
በማዕድን ዘርፍ በተለይም በወርቅ ኤክስፖርት ላይ የታየው የ3320 በመቶ ዕድገት እጅግ አስገራሚ ነው። የድንጋይ ከሰል ምርትም የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከመሸፈን አኳያ በ2010 ከነበረበት 17 በመቶ ተነስተው በ2017 ወደ 75 በመቶ ድርሻ ማሳደግ ተችሏል።
ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል ዓለም በፈጣን እርምጃ እየገባች ነው። የ"ፋይዳ" ዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚዎች 41.5 ሚሊዮን ሲደርሱ፣ የ"ኢትዮ ኮደርስ" ስልጠና 4.5 ሚሊዮን ተሳታፊዎችን አፍርቷል። የዲጂታል ግብይትም ከ12.5 ትሪሊዮን ብር ወደ 24.2 ትሪሊዮን ብር በማደግ የኢኮኖሚውን ቅልጥፍና አረጋግጧል።
በሌላ በኩል፣ "የገበታ" ፕሮጀክቶች የሀገሪቱን የቱሪዝም ገጽታ ቀይረውታል። በዚህም ምክንያት የጎብኝዎች ፍሰት በ2018 ዘጠኝ ወራት ውስጥ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ63 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል።
የልማቱ ማዕከል የሰው ልጅ መሆኑን መንግሥት በተግባር እያረጋገጠ ነው። በጤናው ዘርፍ የእናቶችና ህጻናት ሞት እንዲሁም መቀጨጭ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል። 63 ሚሊዮን ዜጎች የጤና መድህን ተጠቃሚ በመሆናቸው የሕክምና ተደራሽነት ሰፍቷል።
በትምህርት ዘርፍ "ትምህርት ለትውልድ" በተሰኘ ንቅናቄ ከ140 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት በማሰባሰብ የትምህርት ቤቶች ደረጃ ተሻሽሏል። የትምህርት ቤት ምገባ መርሐ ግብርም 46.6 ቢሊዮን ብር በማሰባሰብ ሚሊዮኖችን ተጠቃሚ ከማድረጉም በላይ፣ በአዲስ አበባ ከተማ የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች የማለፍ ምጣኔ ባለፉት 5 ዓመታት ውስጥ በ40 በመቶ እንዲያድግ መሰረት ሆኗል።
እነዚህ እውነታዎች የሚያረጋግጡት አንድ ትልቅ ሀቅ አለ። ይህም የኢትዮጵያ መንግሥት የጀመረው ሁለንተናዊ የሪፎርም ጉዞ ውጤታማ፣ ሳይንሳዊ እና በትክክለኛ ጎዳና ላይ ያለ መሆኑን ነው። ሀገራችን ከውጭ ጥገኝነት አላቅቆ፣ የዜጎችን ማኅበራዊ ተጠቃሚነት አረጋግጦ እና ኢኮኖሚውን በፅኑ መሠረት ላይ ገንብቶ ወደ ብልጽግና ማማ ለማድረስ እየተደረገ ያለው ጥረት ፍሬያማነቱ በተግባር ተረጋግጧል። ይህ ጉዞ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ነገ የሚያሸጋግር የታመነ የብልጽግና ጎዳና ነው።
በአዶኒያስ ወደልአረጋይ